በተደጋጋሚ የሚጠየቁ ጥያቄዎች

የአዲስ አበባ ውሃ ፍሳሽ ባለሥልጣን የሚያመርተውን ውሃ የዓለም ጤና ድርጅት እና የኢትዮጵያ የመጠጥ ውሃ ጥራት ደረጃ ማሟላቱን በማረጋገጥ ለህብረተሰቡ እንዲሰራጭ ያደርጋል፡፡ ይህን የጥራት ደረጃውንም ለማረጋገጥ አስፈላጊውን የጥራት ምርመራ ያከናውናል፡፡

ይህን የመጠጥ ውሃ ጥራት ለማረጋገጥ የማክሮባዮሎጂካል፣ የኬሚካል እና የፊዚካል ምርመራዎችን ያከናውናል፡፡

የማይክሮባዮሎጂካል የውሃ ጥራቱን ለማረጋገጥ ዓመቱን በሙሉ (የዕረፍት እና የበዓላት ቀናትን ጨምሮ) ከውሃ ማጣሪያዎች፣ ከማጠራቀሚያዎችና ከህብረተሰቡ የውሃ ቧንቧዎች በየዕለቱ 30 ናሙናዎችን በመውሰድ የውሃ ጥራት ምርመራ ያከናውናል፡፡ በየዕለቱ የተሰራጨው ውሃም በቂ የክሎሪን ይዘት መያዙን እና በአግባቡ መታከሙን ለማረጋገጥ እንዲሁም የፊዚካል እና የኬሚካል የውሃ ጥራት መስፈርቱን ማሟላቱን ለማረጋገጥ ናሙናዎችን በመውሰድ አስፈላጊውን ምርመራ ያከናውናል፡፡

በዚሁ መሠረትም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የሚያመርተው እና የሚያሠራጨው የመጠጥ ውሃ ማሟላት የሚገባውን የመጠጥ ውሃ የጥራት መስፈርት ማሟላቱ እየተረጋገጠ ለህብረተሰቡ እየቀረበ ይገኛል፡፡

ሆኖም ግን የውሃ መስመር በተለያዩ ምክንያቶች ሲሰበር አፈር እና ሌሎች ባዕድ ነገሮች ሊገቡበት ይችላሉ፡፡ እንዲሁም ረዥም የውሃ ፈረቃ ባለባቸው እና የብረት መስመር ባለባቸው አካባቢዎች ውሃ በመስመር ውስጥ ሳይኖር ሲቀር ብረቱ የመዛግ ባሕርይ ስለሚኖረው ውሃ ሲመጣ ጠራርጎት ስለሚሄድ ስንከፍተው ድፍርስ ውሃም ሊመጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን በቂ የክሎሪን መጠን በውሃ ውስጥ ተሸክሞ ስለሚመጣ ጎጂ ተህዋስያንን ያስወግዳል፡፡ ስለሆነም ከ2-3 ደቂቃ ድፍርስ ውሃ እስኪቆም በማፍሰስ ቀድቶ መጠቀም ይቻላል፡፡

ነገር ግን ሽታ ያለው እና የተለየ መልክ ያለው ውሃ ሲያጋጥም ደንበኞቻችን በ0911862727 በመደወል ጥቆማ ብትሰጡ አፋጣኝ ማስተካከያ እናደርጋልን፡፡

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ከ4 በላይ በሆኑ አማራጮች የውሃ አገልግሎት ክፍያን አቅርቦላችኋል፡፡ በመሆኑም በደንበኛ መለያ ቁጥራችሁ አማካኝነት ወር በገባ ከ26 እስከ 18 ባሉት ቀናት ፡-

  • በማንኛውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በመስኮት በኩል መክፈት ትችላላችሁ፡፡
  • ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የCBE Birr አካውንት በመክፈት እና ብር በማስቀመጥ የትም መሄድ ሳያስፈልጋችሁ በቀላሉ እጃችሁ ላይ ባለው ሞባይል ስልክ አማካኝነት መክፈል ይቻላል፡፡ ለዚህም የባለስልጣኑን መለያ ቁጥር 878787 ይጠቀሙ፡፡ በተጨማሪም አቅራቢያችሁ በሚገኙ የንግድ ባንክ ወኪሎች (ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች፣ ሱፐር ማርኬቶች ወ.ዘ.ተ) አማካኝነት መክፈል ይቻላል፡፡
  • የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ አካውንት በመክፈት (ነባር አካውንትም ይቻላል) እና ባንኩ የውሃ ሂሳባችሁን እየቀነሰ እንዲከፍልላችሁ ፈቃደኝነታችሁን በመግለፅና በመስማማት ሂሳባችሁን እያወቃችሁ ባንኩ ከቁጠባ ሂሳባችሁ ላይ ተቀናሽ እያደረገ እንዲከፍልላችሁ ማድረግ ይቻላል፡፡
  • የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ደንበኞቻችን የባንኩን ኢንተርኔት ባልኪንግ አገልግሎት በመጠቀም ክፍያውን መፈፀም ይቻላል፡፡

ደንበኞቻችን ለተጨማሪ መረጃ አቅራቢያችሁ የሚገኝ የኢትዮያ ንግድ ባንክ በመሄድ ማብራሪያ መጠየቅ ትችላላችሁ፡፡