ባለስልጣኑ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ እና የሰራተኛውን የባለቤትነት ስሜት ለማሳደግ የሚያስችል በዓይነቱ ለየት ያለ የመሪነት ስልጠና ከመስከረም 19/2012 ዓ.ም ጀምሮ እየሰጠ ይገኛል ፡፡

(Field Level Leadership ) ስልጠና የአስተሳሰብ ለውጥ እንደዲያመጡ እንደረዳቸው የተናገሩት ሰልጣኞቹ፤ ከዚህ ቀደም ይህ በሀላፊ እንጂ አይፈታም ያሉት በርካታ ችግር በራሳቸው መፈታት የሚችል መሆኑን የተረዱበት፤ ይህንኑ ተግባራዊ በማድረግ እና ደንበኛን እንደ ቤተሰብ በመያዝ ለባለስልጣኑ አምባሳደር ለመሆን እንደተዘገጁ ገልጸዋል፡፡

ሰልጣኞቹ አክለውም ‹‹እኔ በዚህ ስልጠና በመጀመሪያ ራሴን ቀይሪያለሁ፡፡ ቀጥሎ ልጆቼንና ቤተሰቤን ቀይራለሁ፡፡ ከዚያም አብረውኝ የሚሰሩ ባልደረቦቼን የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ተቋሜን ብሎም ሃገሬን በአገልግሎት አሰጣጥ ለማሳደግ እሰራለሁ ብለዋል፡፡

ስልጠናው የአፈፃፀም አቅምን በመገንባት ሠራተኞች በእኔነት ስሜት የሚመሩት ዘላቂ የሆነ ለውጥ ለመፍጠር ብሎም የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ አጋዥ እንደሆነ ታምኖበት ነው የተጀመረው ፡፡

የአቅም ግንባታ ስልጠናውን ከግብ ለማድረስ 20 ባለሙዎች እና ሃላፊዎች በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ለአስር ተከታታይ ቀናት በህንድ ሃገር የአሰልጣኞች ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል ፡፡

በዚህም መሰረት በመጀመሪያ ዙር የአራዳ እና የአዲስ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ስድስት መቶ ሠራተኞች በ20 ዙር ለገዳዲ በሚገኘው የባለስልጣኑ ማሠልጠኛ ማዕከል ገብተው እየሰለጠኑ ሲሆን እስካሁንም በስድስት ዙር 180 ሰራተኞች ሰልጥነዋል፡፡

በቀጣይም ሁሉም የባለስልጣኑ ቅ/ጽ/ቤት ሠራተኞች በሁለት ዓመት ውስጥ አሠልጥኖ ለመጨረስ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡

ስልጠናው በአለም ባንክ፣ በቪቴንስ ኢቪደንስ ኢንተርናሽናል እና በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን ከዚህ በፊት በአለም ባንክ ግሎባል ኢንሸቲቭ በህንድ እና በታንዛኒያ ተሰርቶበት ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ነው፡፡