የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን  በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የቆጣሪ ንባብ  ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገለጸ፡፡ ቴክኖሌጂውም ዳፍቴክ ሶሻል አይ.ሲ.ቲ. ከተባለ የግል ድርጅት  ጋር ከባለስልጣኑ ውል በመግባት ወደ ስራ ተገብቷል፡፡

የቆጣሪ ንባብ የሚካሄደው በስማርት ተንቀሳቃሽ ስልኮች ሲሆን ለስልኮቹ የቆጣሪ ማንበብያ አፕልኬሽን ሲሰተም የተጫነላቸው ሲሆን ለዚህም ስራ የሚረዱ 264 ስማርት ተንቀሳቃሽ ግዢ ተፈጽሟል፡፡

አዲሱ የቴክኖሌጂ ግብዓት መጠቀም በአጭር ጊዜ የብዙ ደንበኞች ቆጣሪ ማንበብ ከማስቻሉ በተጨማሪ ከዚህ በፊት ከቆጣሪ ንባብ ጥራት ጋር  ተያይዞ የሚገጥሙ ችግሮችን የሚፈታ ስለሆነ የተመረተውና የተሸጠው ውሃ ሪፖርት ትክክለኛ እንዲሆን ስለሚረዳ ለወደፊት ባላስልጣኑ የውሃ ብክነትን ለመቀነስ የሚሰራው ስራ አጋዥ ይሆናል፡፡

ቴክኖሎጂው በጂ.ፒ.ኤስ የሚሰራ በመሆኑ የኢትዮ ቴሌ ኮም ኔትወርክን አይጠቀምም፡፡ በተጨማሪም ከቆጣሪው በ2 ሜትር ርቀት ውስጥ ካልተገኙ በስተቀር ኔትወርኩ የማይሰራ በመሆኑ ቆጣሪ አንባቢው በአካል ተገኝቶ እንዲያነብ የሚያሰግድድ ይሆናል፡፡

በቆጣሪ ንባብ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ ከስምንቱም ቅ/ጽ/ቤቶች የተወጣጡ ከ200 በላይ ቆጣሪ አንባቢዎች የንድፈ ሀሳብ እና የተግባር ላይ ስልጠና የተሰጣቸው ሲሆን ቴክኖሎጂውም ከሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል፡፡