በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ደንበኞች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ክፍያ መፈጸም የሚያስችላቸውን ስምምነት  አደረገ፡፡

በስምምነቱ መሰረት ባንኩ በከተማዋ ለሚገኙ የውሃ ደንበኞች በአራት አይነት የአከፋፈል ስርዓት ማለትም በሞባይል ባንኪንግ፣ በኢንተርኔት ባንኪንግ፣ ከተቀማጭ በሚቀነስ ሂሳብ እና በባንኩ ቅርንጫፎች አማካኝነት አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል፡፡

ደንበኞች በባንኩ መስኮት ለሚያገኙት አገልግሎት ብቻ 2 ብር ክፍያ የሚፈፅሙ ሲሆን በተቀሩት አገልግሎቶች ግን ምንም አይነት ክፍያ አይጠየቁም፡፡

የተደረገው ስምምነት ደንበኞች በዘመናዊ የክፍያ ስርዓቶች ላገኙት የውሃ አገልግሎት ክፍያ እንዲፈፅሙ ከማስቻሉም በላይ በከተማው ውስጥ በሚገኙ ከ300 በላይ የባንኩ ቅርንጫፎች አማካኝነት የመስኮት አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ የደንበኞችን ጊዜ እና እንግልት የሚቀርፍ ይሆናል፡፡

ስምምነቱን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ዘሪሁን አባተ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ስራ አሰፈጻሚ አቶ ባጫ ጊና  ፈርመዋል፡፡

ባለስልጣኑ ከሐምሌ 30/2011 ዓ.ም ጀምሮ ከለሁሉ ክፍያ ጣቢያ ጋር የነበረውን ስምምነት ያቋረጠ ሲሆን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያደረገው ስምምንት ከነሐሴ/ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለቀጣይ ሶስት አመት የሚቆይ ይሆናል፡፡

ዝርዝር የክፍያ አፈፃፀምን በተመለከተ ባለስልጣኑ በቀጣይ ተከታታይ መረጃዎችን ለደንበኞቹ የሚያደርስ ይሆናል፡፡