ባለስልጣን መ/ቤቱ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የሚያቀርበውን ንጹህ  ውሃ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለማሰራጨት እንዲቻል ለከፍተኛ ውሃ ተጠቃሚዎች የሚያቀርበውን የውሃ መጠን በመቀነስ ወደ ህዝቡ የሚያሰራጨውን የውሃ መጠን እንዲጨምር ለማድረግ ከፍተኛ ውሃ ተጠቃሚ ደንበኞች የራሳቸውን አማራጭ የውሃ መገኛ እንዲያጎለብቱ እና እንዲጠቀሙ ለማድረግ የሚያስችል  መመሪያ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን የስርጭት እና  ሲስተም ቁጥጥር የስራ ሂደት መሪ  የሆኑት አቶ ታደሰ ዘገየ ገልጸዋል፡፡

ባለስልጣኑ ያለውን የውሃ ዕጥረት ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍትሃዊ የውሃ ስርጭት እንዲኖር ከፍተኛ የውሃ ተጠቃሚዎች የራሳቸውን ጉድጓድ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ዕቅድ ነድፎ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅሰቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ የራሳቸው ጉድጓግ ያላቸውን ተቋማት የመለየት ስራ ተሰርቷል፡፡ አቶ ታደሰ እንደገለጹት ከቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጋር በመተባበር በተደረገው የዳሰሳ ጥናት አገልግሎት የሚሠጡ 177 ጎድጉዶች ያሏቸው 157 ተቋማት የተለዩ ሲሆን 16 ያህል ጉድጓዶች ደግሞ በኤሌክትሮ መካኒካል ብልሽት ምክኒያት የቆሙ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ እንደ አቶ ታደሰ ማብራሪያ 9 ያህል ጉድጓዶች  በውሃ ጥራት ችግርምክኒያት እንዲሁም 16 ያህል ጉድጓዶች በመንጠፍ ምክኒያት አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ተገልቷል፡፡

አቶ ታደሰ አያይዘውም ከፍተኛ ተቋማት የራሳቸውን ጉድጓግ በመጠቀም የውሃ አቅርቦቱ ላይ የሚያደርሱትን ጫና በመቀነስ የውሃ ስርጭቱ ፍትሃዊ ይሆን ዘንድ ጉድጓድ ላላቸውና ለወደፊቱም ለሚቆፍሩ ተቋማት የቴክኒክ ድጋፍ ከመስጠጥ ጀምሮ እስከማማከር የሚዘልቅ ድጋፍ ለመስጠት መታሰቡን እና የተለዩ ከፍተኛ የውሃ መጠን ተጠቃሚዎች የራሳችው ጉድጓድ እንዲጠቀሙ የሚያበረታታ አሰራር በመዘርጋት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡