የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሠራተኞች የአንድ ቀን ደመወዛቸው  በማሰባሰብ  ጨቢ ማሪያም  የለገዳዲ እና  ድሬ ግድቦች ዙሪያ ለሚገኙ የጨቢ ማርያም እና ድሬ ስኮሩ የመጀመሪ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ255 ሺህ ብር በላይ የገዟቸውን ልዩ ልዩ የትምህርት መርጃ መሳሪዎች አበርክተዋል፡፡

በድጋፍ የተሰጡት ቁሳቁሶች ደብተር፣ እስኪቢርቶ፣ እርሳስ፣ ማስመሪያ እንዲሁም የእርሳስ መቅረጫዎች እና ላጲስ ናቸው፡፡

የወረዳው አስተዳደር፣ ወላጆች፣ መምህራን እና ተማሪዎች በተገኙበት የትምህርት ቁሳቁሶቹን ያበረከቱት የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪጅ ኢንጂነር ዘሪሁን አባተ  የሰው ልጅ ከድህነት እና ኋላ ቀርነት ለመውጣት ቁልፉ መሣሪያ ትምህርት በመሆኑ ተማሪዎች ጠንክረው መማር እንደሚኖርባቸው አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም በውሃ መገኛ አካባቢዎች ለሚገኙ በዝቅተኛ ደረጃ ላሉ ተማሪዎች የትምህርት መረጃ መሣሪያ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥሉ የገለጹት ኢንጂነር ዘሪሁን  በዚህ በጐ ተግባር የተሳተፉ የባለሥልጣኑን ሠራተኞች አመስግነዋል፡፡

በእለቱ የተገኙ እና አስተያየታቸውን የሰጡ ወላጆችም የባለስልጣኑን ሠራተኞች ላደረጉት ድጋፍ  አመስግነው ልጆቻቸውን በትምህረታቸው ጠንካራ እንዲሆኑ ከመከታተል ባለፈ  የአካባቢ ጥበቃ ላይ በንቃት በመሳተፍ  ለውሃ ሀብቶቹ  ቀጣይነት  የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ገልፀዋል፡፡