የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የኤሌክትሮ ሜካኒካልና ብየዳ ሥራዎች ንዑስ የስራ ሂደት የካይዘን ፍልስፍናን ወደ ተግባር በመቀየር 1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስቀረ ውሃ ፓምፕና ሞተሮችን ለመፈተሽ የሚያስችል ቴስት ቤንች የተባለ አንድ መፈተሻ ማሽን ሰራ፡፡

ክፍሉ መፈተሻ ማሽኑን የሰራው  አገልግሎት ላይ የዋሉ የተለያዩ ዕቃዎችን በማሰባሰብ ነው፡፡

መፈተሻው ጠላቂ የውሃ ፓምፕና ሞተሮች ወደ ውሃ መገኛ ጣቢያ ተወስደው የጉድጓድ ውሃ ፓምፕ ውስጥ ከመተከላቸው በፊት ፓምፑ በሚፈለገው የግፊት መጠን  የሚጠበቅበትን የውሃ ብዛት (Discharge) መስጠቱን ለማወቅ ከማገዙም በላይ፤ የሞተርና ፓዎር ኬብል ቮልካናይዝ ከተደረጉ በኋላ ውሃ ወደ ኤሌክትሪክ ገመዱ አለመግባቱን  ለማረጋገጥ ይረዳል፡፡

በስራ ክፍሉ ሲኒየር መሐንዲስ አቶ አድማሱ አሰፋ እንዳሉት ፓምፑ ወደ ጉድጓድ ውሃ ከመግባቱ በፊት  እነዚህን ፍተሻዎች ማድረጉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡

ይኸውም ፓምፕና ሞተሩ ወደ ውሃ ጉድጓድ ከገባ በኋላ የቴክኒክ ችግር በመኖሩ ፓምፑን ማሰራት ባይቻል እንኳ ፓምፑን፣ ሞተሩንና ፓወር ኬብሉን ማውጣትና ችግሩን ለይቶ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ደግሞ ለክሬንና ለሠራተኛ ወጪ ከመዳረጉም በላይ ተጠግኖ ወደ ስራ ለማስገባ ረጅም ጊዜን የሚወስድ አድካሚ ስራ ነበር፡፡

አሁን ግን በክፍሉ በተሰራው ቴስት ቤንች አማካይነት ማሽኑ ላይ የተሞከረ ፓምፕና ሞተር ውሃ ጉድጓድ በማስገባት የተጠቀሱትን ችግሮች ለመቅረፍ እንደሚያስችል ነው አቶ አድማሱ የተናሩት፡፡

ችግር ያለባቸውን ፓምፕና ሞተሮች በቴስት ቤንች ሙከራ መለየት፣ የጥገና ወይም የማስተካከል ስራ መስራት፣ የተቃጠሉ ሞተሮችን መልሶ አገልግሎት ላይ እንዲዉሉ የተደረጉ ሞተሮችን አፈጻጸም  መፈተሽም የቴስት ቤንቹ ቱሩፋቶች ናቸው ፡፡