የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለስልጣን የኮሌራ በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል በውሃ ስርጭት እና በፍሳሽ አወጋገዱ ላይ ከወትሮ በተለየ መልኩ በጥንቃቄ እየሰራ ነው፡፡

በተለያዩ አከባቢዎች የተከሰተው የኮሌራ/አተት/ በሽታ በከተማችን ከውሃ ስርጭት ጋር በተገናኘ እንዳይከሰት ባለስልጣኑ በሚያሰራጨው ውሃ ላይ የክሎሪን መጠኑን ጨምሯል፡፡

ባለስልጣኑ በየዕለቱ የላቦራቶሪ ምርመራውን ለማካሄድ በከተማ ውስጥ ከየአካባቢው የሚወስደውን የውሃ ናሙና ቁጥር ከ 30 ወደ 40 ከፍ በማድረግ የውሃ ጥራት ቁጥጥሩን ይበልጥ አጠናክሯል፡፡

በመስመር ስብራት ምክንያት ውሃ እንዳይበከል ባለስልጣኑ ለዚሁ ዓላማ ባቋቋመው ግብረ-ኃይል አማካይነት ጥብቅ ክትትል በማድረግ አፋጣኝ ጥገና እንዲካሄድ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እጥረት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ላይ ለሚቀመጡ ሮቶዎች እና ለውሃ ማጓጓዣ ቦቴዎች የሚደረገውን የእጥበት አገልግሎት ከሶስት ወር ወደ አንድ ወር ዝቅ በማድረግ ንፅህናቸው ይበልጥ አስተማማኝ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

ጥቂት የማይባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በሚገኙባቸው እና ንክኪ በሚበዛባቸው እንደ ማረሚያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ የህፃናት ማሳደጊያዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና የመሳሰሉት ተቋማት ላይ የሞሉ መፀዳጃ ቤቶች ካሉ ፍሳሾች ከመገንፈላቸው በፊት ቅድሚያ በመስጠት እየተነሳላቸው ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ የበኩሉን ጥንቃቄ ማድረግ ስለሚኖርበት የውሃ ማስቀመጫ ዕቃዎችን ንፅህና በአግባቡ መጠበቅ እና የሞሉ መፀዳጃ ቤቶች ካሉ ከመፍሰሳቸው በፊት በአፋጣኝ ማስነሳት፤ የውሃ መስመር ስብራት ሲያጋጥም ጥገና እንዲካሄድ በነፃ የስልክ መስመር 906 ላይ በመደወል እና በሚገለገሉበት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በአካል ተገኝተው ጥቆማ መስጠት እንደሚችሉ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለስልጣን ያሳስባል፡፡