በመዲናችን አዲስ አበባ ፍሳሽ ቆሻሻን የማስወገድ አገልግሎት የጀመረው በ1920ዎቹ መጨረሻ ገደማ ነው፡፡ ጅማሮው በ1920ዎቹ ይሁን እንጂ፣ ፍሳሽን በዘመናዊ መልኩ በመስመር የማስወገድ ሥራው ከቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታ መጠናቀቅ ጋር ተያይዞ በ1974 ዓ.ም ተግባራዊ እንደተደረገ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በመቀጠልም በ1993 በቀን 3,000 ሜትር ኪዩብ ፍሳሽ የመቀበል አቅም ያለው የኮተቤ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡

ባለሥልጣን መ/ቤቱ የፍሳሽ ማስተላለፊያ መሥመር በመዘርጋትና ማጣሪያ ጣቢያዎችን በመገንባት እንዲሁም በተሽከርካሪ በማንሳት የሚያከናውነውን ተግባራት ከጊዜ ጊዜ እያሳደገ በመሄድ ላይ ነው፡፡ በቀን 100,000 ሜ.ኩ የማጣራት አቅም ያለውና በቅርቡ ተመርቆ ስራ የጀመረው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ የዚህ ማሳያ ነው፡፡ በግዙፍነቱ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የሆነውና 1.5 ሚሊየን የከተማዋን ነዋሪ ተጠቃሚ የሚያደርገው ይህ ፕሮጀክት ግንባታው ተጠናቆ ከተመረቀ በኋላ አዳዲስ የመስመር ቅጥያዎች እየተከናወኑ ሲሆን፣ ከማጣሪያ ጣቢያው የሚለቀቀው ውሃ አካባቢን የማይበክል እና በታችኛው ተፋሰስ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚጠቅም ከመሆኑ ባሻገር ውሃው ወደ መሬት እንዲሰርግ በማድረግ ግልጋሎት እየሰጡ ያሉት የከርሰ ምድር ጉድጓዶቻችን ምርታቸው እንዳይቀንስ በማገዝ በኩል ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

ማጣሪያ ጣቢያ በሙሉ አቅሙ በቀን 100 ሺህ ሜትር ኩብ ማጣራት ሲጀምር ወደ ወንዝ በሚለቀቀው ውሃ ወደፊት፡-

Þ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ለመስራት፣

Þ ለመስኖ ልማት፣

Þ ለግንባታ አገልግሎት እንዲሁም

Þ ለከተማ ግብርና ጥቅም ላይ ማዋል ያስችላል፡፡

ከማጣሪያ ጣቢያው የሚገኘው ተረፈ ምርትም ማዳበሪያ ለማምረት እና ከባዮ ጋዝ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ይጠቅማል፡፡ ይኼንንም ተግባራዊ ለማድረግ ባለስልጣኑ እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓት ከማሕበረሰብ ጤና ጋር ያለው ቁርኝት ከፍተኛ በመሆኑ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት በጀመሩት በዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አማካይነት

î የመሰብሰብ፣

î የማጓጓዝ፣

î የማጣራት፣

î መልሶ የመጠቀም እና

î የማይፈለገውን ደግሞ አካባቢውን በማይበክል መልኩ የማስወገድ ኃላፊቱን ባለስልጣኑ እየተወጣ ቢሆንም የከተማዋን ነዋሪዎች የዘመናዊ የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓት ተጠቃሚ እያደረጉ የሚገኙት የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች እና የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ለአደጋ እየተጋለጡ ነው፡፡

î ማጣሪያ ጣቢያዎቹን እና የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮቹን ለአደጋ የሚያጋልጡ ዋነኛ ተግባራት የሚፈፀሙት በተገልጋዩ የህብረተሰብ ክፍል የግንዛቤ ማነስ የተነሳ ሲሆን ወደ መፀዳጃ ቤቶች የሚጥሏቸው ባዕድ ነገሮች  በፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮች እና በፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ላይ ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ባዕድ ነገሮች ተብለው የተለዩ እንደ፡-

– ዳይፐር 

– ጨርቃ ጨርቅ

– አጥንት

– የእንስሳት አንጀት

– ደረቅ ቆሻሻ

– ፔስታል እና

የመሳሰሉት ጠጣር ነገሮች ሲሆኑ፣ እነዚህ ጠጣርና ባዕድ ነገሮች የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን በመዝጋት እክል ይፈጥራሉ፡፡ የአወጋገድ ሂደቱንም ያስተጓጉላሉ፡፡ እነዚህ ባዕድ ነገሮች ፍሳሽ ቆሻሻ የማጓጓዝ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት መስመሮች ስለሚዘጉ ፍሳሽ ቆሻሻዎች ገንፍለው እንዲወጡ በማድረግ አካባቢን ከመበከል ባለፈ ለከተማዋ ነዋሪዎች የጤና ጠንቅ በመሆን ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ከየቤቱ እና ከፋብሪካዎች የሚለቀቁ ቅባት ነክ ነገሮች የማጣሪያ ጣቢያዎችን ለብልሽት እያደረጉት ሲሆን፣ ቱቦዎች ላይ ተከማችተው የፍሳሽ ማስተላለፊያ  መስመርን ከማጥበብ ባለፈ እስከ መድፈን በማድረስ ገንፍለው በመውጣት አካባቢን ለብክልት በመደረግ ላይ ናቸው፡፡ ህብረተሰቡም በዚህ ምክንያት ለጤና መታወክ በመጋለጡ በባለስልጣን መ/ቤቱ ላይ ቅሬታ በማሰማት ላይ ይገኛል፡፡ የሚቀርቡ ቅሬታዎች መፍታትም ሆነ ማጣሪያ ጣቢያዎችን ከአደጋ መታደግ የሚቻለው ህብረተሰቡ በሚያሳየው ትብብር ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የከተማዋ ነዋሪዎች የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎችን እና የማስወገጃ መስመሮችን ለብልሽት የሚዳርጉ ከላይ የተጠቀሱ ተግባራትን ሊቆጠብ ይገባል፡፡