ከህብረተሰቡ መዘናጋት ጋር ተያይዞ እየተቀዛቀዘ የመጣውን እና እንደ አዲስ እያንሰራራ የሚገኘውን የኤች አይ ቪ ኤድስ ወረርሽኝ በማስመልከት “አሁንም ትኩረት ለኤች አይ ቪ ኤድስ” በሚል መሪ ቃል በባለስልጣኑ የኤች አይ ቪ ኤድስ ግብረ ኃይል ስልጠና ተዘጋጅቶ በዋናው መ/ቤት የግማሽ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷል፡፡ በስልጠናው ላይ ጥናታዊ ፅሑፍ ቀርቦ ከሰራተኛው ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

የጥናቱ አቅራቢ የፕሮጀክት ጥናትና የኃብት ማሰባሰብ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ አበራ ገመቹ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ባላገቡ ወጣቶች ላይ በተለይም በሴቶች ላይ ልቆ እንደሚስተዋል ገልፀው በሃገራችን ኢትዮጵያ በየዓመቱ ሰላሳ ሺህ ህዝብ በቫይረሱ እንደሚያዝና 20 ሺህ ተጠቂዎች ለሞት እንደሚዳረጉ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የህ/ሰብ ክፍሎች ምርመራ አድርገው ራሳቸውን ባለማወቃቸው ቫይረሱን እያዛመቱ እንደሚገኙ እና ይበልጥ እየተጎዱ ያሉት ደግሞ ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ የሌላቸው በተለያዩ ሱሶች የተጠመዱ ወጣቶች መሆናቸው ሁኔታውን አሳሳቢ ያደርገዋል ሲሉ አቶ አበራ ገመቹ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ከቀረበው የጥናት ሰነድ መረዳት እንደተቻለው በአስተዳደግ ረገድ የቤተሰብ ቁጥጥር መላላትና ክትትል ማነስ ብሎም የጫት ቤቶች፣ የሺሻ ቤቶች እና የምሽት ቤቶች መስፋፋት ችግሩን አባብሰውታል፡፡ የቫይረሱ መስፋፋትም ከክልል ክልል የሚለያይ ሲሆን፣ በከተሞች አካባቢ በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ ስርጭቱ እየተባባሰ እንደሄደና  የዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ከተሞች በባህሪያቸው ውስብስብ ከመሆናቸው ጋር ተያያዞ ስሜት ቀስቃሽ ትዕይንቶች በመበራከታቸው መሆኑ መገንዘብ ተችሏል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ፣ መድኃኒቱን ማቋረጥም ሆነ መድኃኒቱን አለመጀመር የቫይረሱን መጠን እንዲጨምር ከማድረጉም ባሻገር በዚህ ምክንያት ለአልጋ ቁራኛ የተዳረጉ በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በከተማችን መኖራቸው ተገልጿል፡፡

“የቫይረሱን መጠን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመቆጣጠር ተመርምሮ ራስን በማወቅ ብሎም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ለችግሩ ዋነኛ መፍትሔ መሆኑን በመረዳት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ይህን መርህ በመከተል የድርሻውን ማበርከት እንደሚጠበቅበት የጥናቱ አቅራቢ አቶ አበራ ገመቹ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የባለስልጣኑ የስርዓተ ፆታ ዴስክ ኃላፊ ወሮ አልማዝ ኤጀርሳ በበኩላቸው በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን በመርዳትና በቫይረሱ ለተያዙ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል” ብለዋል፡፡