በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ ሁለት ጀሞ ቁጥር አንድ ኮንዶምኒየም አከባቢ ከመኖሪያ ቤቶች የሚወጣ ፍሳሽን አሰባስቦ ለማስወገድ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ የፍሳሽ መስመር በመንገድ ግንባ ቁፋሮ አማካኝነት ከጥቅም ውጪ ሆነ፡፡ ፕሮጀክቱ የግንባታ ስራው ተጠናቆ ሙከራ የተደረገለት ሲሆን ጉዳት የደረሰበት ርክክብ ለማድረግ በተዘጋጀበት ወቅት ነው ፡፡

የፍሳሽ ማንሳት፣ ማጣራት እና መልሶ መጠቀም አብይ የስራ ሂደት መሪ የሆኑት ወ/ሮ ጀሚላ መሃመድ እንደገለፁት ጉዳት የደረሰበት የነፋስ ስልክ ላፍቶ ወረዳ 2 የፍሳሽ መስመር 402 ደንበኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ቅጥያ የተሰራለት እና ከ2,500 በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ የመሰረተ ልማት ስራዎች ሲሰሩ ቅንጅታዊ አሰራር መኖር የግድ አስፈላጊ መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ ጀሚላ የመንገድ ግንባታው ሲሰራ ከውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ጋር  የመረጃ ልውውጥ ቢደረግና በመናበብ ቢሰራ የደረሰውን ጉዳት ማዳን ይቻል ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን የፍሳሽ መስመሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ብሏል፡፡

የከፍተኛ ፍሳሽ መስመር ዝርጋታና ጥገና ንዑስ የስራ ሂደት መሪ የሆኑት ወ/ሪት ፀጋ ወ/ስላሴ በበኩላቸው ዘመናዊ የፍሳሽ መስመሩ በህብረተሰቡ ተደጋጋሚ ጥያቄ መሰራቱን ገልፀው ህብረተሰቡ ተጠቃሚ በሚሆንበት ወቅት ሊጠገን በማይችል ሁኔታ ከጥቅም ውጭ በመሆኑ በባለስልጣኑ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር ፈጥሯል፡፡

በንፋስ ስልክ ቅርንጫፍ የውሃ ስርጭትና ጥገና አገልግሎት ሲኒየር ቴክኒሺያን የሆኑት አቶ አብይ ቤሌማ ጉዳት የደረሰው በፍሳሽ መስመር ላይ ብቻ ሳይሆን በውሃ መስመር ላይም በመሆኑ በመስመሩ ላይ ጥገና ለማድረግ መቸገራቸውን እና ህብረተሰቡም ቅሬታ በማሰማት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የፍሳሽ መስመሩ ሰኔ 2009 ዓ.ም የተጀመረና በቀን 100 ሺ ሜትር ኩብ ለሚያጣራው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ የመኖሪያ ቤት ፍሳሽን የሚያሰባስብ ፕሮጀክት ነበር፡፡