ፕሮጀክቱ ከሁለት ዓመት በፊት ተጀምሮ በውጭ ምንዛሬ ፣ የወሰን ማስከበር  እና የዲዛየን ክለሳ ችግር ተቋርጦ የነበረ ሲሆን  በአሁኑ ሰአት ያለበትን ችግር በመፍታት ግንባታው እየተፋጠነ ይገኛል፡፡

የውሃ ፕሮጀክቱ በቀን 68ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ የማምረት አቅም ኖሮት 618 ሺህ የከተማውን ነዋሪ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀረጸ ፕሮጀክት ነው ፡፡

በአሁኑ ሰዓትም በፕሮጀክቱ የታቀፉ የ21 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን ቁፋሮ ተጠናቀቆ በቂ ውሃ ተገኝቷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በ12ቱ ጉድጓዶች ላይ የፓምፕ ሀውስ ፣የጥበቃ እና ሌሎች ተያያዥ ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን በባለስልጣኑ  ፕሮጀክት ጽ/ቤት የውሃ ግንባታ ቁጥጥር ና የውል አስተዳደር ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ታምራት ፈጠን ተናግረዋል፡፡

የዚህ ፕሮጀክት አንድ አካል የሆነው ባለ 5000 እና 10,000ሜ.ኩብ ውኃ የመያዝ አቅም ያላቸው 4ት ማጠራቀሚያ ጋን ግንባታ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቋል፡፡

ፕሮጀክቱ የ24 ኪ.ሜ ዋና መስመር እና 42 ኪ.ሜ የማሰባሰቢያ መስመር ዝርጋታን የሚያካትት ሲሆን ከዚህም የ7.5 ኪ.ሜ የመስመር ዝርጋታ ስራ ተከናውኗል፡፡

በቀጣይም የኤሌክትሮ ሜካኒካል እቃ አቅርቦት እና ተከላ ብሎም ሌሎች ተያያዥ ስራችን በማጠናቀቅ በ2012 መጀመሪያ ወደ ምርት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የፕሮጀክቱ አማካሪ ድርጅት የኦሮሚያ ውሃ ስራዎች ዲዛየን እና ቁጥጥር ገልጸል፡፡