ባለስልጣኑ ከባለፉት 10 ዓመታት ጀምሮ የከተማዋን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሳደግ እና የህብረተሰቡን ፍላጎት በአግባቡ ለማሟላት ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ያከናወነ ሲሆን፣ ነባር እና አዳዲስ የከርሠ ምድርና የገፀ ምድር የውሃ መገኛ ምንጮችን በማስፋፋት ሰፊ ሥራ ሰርቷል፡፡

ከከተማ አስተዳደሩ፣ ከመንግስት፣ ከአለም ባንክ እና ከቻይና ኤግዚም ባንክ እንዲሁም ከተለያዩ የውጭ አካላት በተገኘ ብድር የተገነቡት ፕሮጀክቶች የገፀ ምድር ማስፋፊያ እና የከርሰ ምድር ቁፋሮዎች ሲሆኑ፣ የከተማዋን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በማሳደግ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡

ከተከናወኑ ዋና ዋና ፕሮጀክቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ የገፈርሳ ግድብ ማሻሻያ፣ የለገዳዲ ግድብ ማስፋፊያ፣ በቀን 50ሺህ ሜ.ኩብ ውኃ የሚያመርተው የኮዬ ፈጬና ቅሊንጦ ኮንዶሚኒየም አካባቢ የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት እና የውኃ ዕጥረት በሚታይባቸው የተለያዩ የከተማዋ ኪስ ቦታዎች (Pocket Area) የጉድጓድ ቁፋሮ ፕሮጀክት እና ሌሎች በመከናወን ላይ የሚገኙ የከርሰ ምድር ውኃ ልማት ፕሮጀክቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዋነኝነት በጥናት ከተለዩ 4 ዌል ፊልዶች በተጨማሪ በአጭር ጊዜ ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡና የተጀመረውን ልማት ማስቀጠል የሚያስችሉ የተለያዩ የከርሰ ምድር ውኃ ልማት ፕሮጀክቶች ተቀርጸው በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪም በቀን 73ሺህ ሜ.ኩብ ውኃ ማምረት የሚያስችለው የገርቢ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት እና በቀን 428 ሺህ ሜ.ኩብ ውኃ ማምረት የሚያስችለው በቀን 68 ሺህ ሜ.ኪ. የሚያመርተው አያት ኖርዝ ፋንታ ግንባታ ሲጠናቀቅ የባለስልጣኑን ውሃ የማምረት አቅም በቀን ከ1,000,000 ሜ.ኩ በላይ ከፍ በማድረግ በተለይም በሰሜኑ የከተማዋ ክፍል የሚስተዋለውን የውሃ ችግር በመፍታት ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል፡፡