የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣንን ለ42 ዓመታት በተለያዩ ሃላፊነቶች ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ እምሩ መኮንን ባደረባቸው ህመም ምክንያት በ70 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

አቶ እምሩ ከአባታቸው አቶ መኮንን ንጉሴ እና ከእናታቸው ወ/ሮ አድጋልኝ ቦጋለ በቀድሞው ወለጋ ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ ምስራቅ ወለጋ ነቀምት ከተማ ኮኒሳ ቀሌ 01 ቀበሌ በሰኔ ወር 1942 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡

የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በነቀምት ወንጌላዊት ሚሲዮን እና በነቀምት ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል፡፡

በመቀጠልም በ1962 ዓ.ም በሀረማያ ኮሌጅ ለ1 ዓመት እንዲሁም ከ1964 ዓ.ም ጀምሮ በፈረንሳይ መንግስት እና በአዲስ አበባ መዘጋጃ ቤት ስር ሲተዳደር በነበረው ቴክኒካል ኮሌጅ ለ4 ዓመታት የምህንድስና ትምህርት ተከታትለዋል፡፡

አቶ እምሩ በ1968 ዓ.ም በዕድገት በህብረት ዘመቻ ከለገዳዲ ግድብ እስከ ኮተቤ የውሃ ማጠራቀሚያ የሚያደርሰውን ከባድ የውሃ መስመር አቅጣጫ ቀይሰዋል፡፡

ከየካቲት 1969 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 1970 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤትም በመሬት ይዞታና ሽንሸና ውስጥ አገልግለዋል፡፡

አቶ እምሩ ከነሐሴ 15 ቀን 1970 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በቴክኒሻንነት፣ በንድፍ ቅየሳ እንዲሁም በኤሌክትሮ መካኒካል መሃንዲስነት ከማገልገላቸው በተጨማሪ የለገዳዲ ውሃ ማጣሪያ ጣቢያ ሃላፊ እና የገፀ-ምድር ውሃ ምርት አቅራቢ ቡድን ኬዝ ማናጀር በመሆን ስራቸውን በከፍተኛ ብቃት እና ሃላፊነት ያከናወኑ ምስጉን ሰራተኛ ነበሩ፡፡

አቶ እምሩ በውሃ መስመር ዝርጋታ ጥናትና በውሃ ሜትዶሎጂ መረጃ ስብሰባ በርካታ ስራዎችን አከናወነዋል፡፡

በተጨማሪም የገፈርሳ እና የለገዳዲ ግድቦችን የማምረት አቅም በማሳደግ ስራዎች ላይ የኤሌክትሮ መካኒካል ሱፐርቫይዘር በመሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

አቶ እምሩ በቤተሰባዊ ህይወታቸው በ1977 ዓ.ም ከወ/ሮ ፅጌረዳ አሠፋ ጋር ትዳር መስርተው 4 ሴቶች እና 1 ወንድ ልጅ አፍርተዋል፡፡

የቀብር ስነ ስርዓታቸውም በነገው ዕለት ማለትም ጥር 3 ቀን 2012 ዓ.ም በለገዳዲ መንበረ እየሱስ ቤተክርስቲን ከቀኑ 6፡00 ላይ ይፈፀማል፡፡

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በአቶ እምሩ መኮንን ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፀ ለስራ ባልደረቦቻቸው ፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ይመኛል፡፡