የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ከገፀ-ምድር እና ከርሰ-ምድር የሚያመርተውን የተጣራ ንፁህ ውሃ ለተጠቃሚው ለማድረስ ከ8 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የውሃ መስመሮችን ዘርግቷል፡፡ ንፁህ የመጠጥ ውሃ በእነዚህ መስመሮች አማካኝነት ደንበኞች ጋር የሚደርሰው በርካታ ማጠራቀሚያዎችን እና ግፊት መስጫዎችን አልፎ ነው፡፡

በከተማዋ ውስጥ በአጠቃላይ 90 የውሃ ማጠራቀሚ እና ግፊት መስጫ ጣቢያዎች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ 55ቱ የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖች፣ 33ቱ የውሃ ማጠራቀሚያ እና ግፊት መስጫ ጣቢያዎች እንዲሁም ሁለቱ ግፊት መስጫ ጣቢያዎች ናቸው፡፡

በዚህ የቅብብሎሽ ሂደት ውስጥ በተለይ በውሃ ማምረቻ እና ግፊት መስጫ ቦታዎች ላይ የኤሌክትሪክ ሃይል መቋረጥ ቢከሰት የውሃ ስርጭቱ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ ከባድ ነው፡፡

ለምሳሌ፡- ከለገዳዲ የሚመረተው ውሃ ሽሮ ሜዳ፣ ፈረንሳይ እና ድል በር ለመድረስ ከ8 ጊዜ በላይ ይገፋል፡፡ በዚህም ከለገዳዲ ወደ ተርሚናል፣ ከተርሚናል ጃን ሜዳ፣ ከጃንሜዳ ተፈሪ መኮንን፣ ከተፈሪ መኮንን ሽሮ ሜዳ፣ ከዚያም አር1…፣አር2.. አር3 እያለ በግፊት እና በቅብብሎሽ ይጓዛል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ከአቃቂ ጉድጓዶች ተሠባስቦ ወደ GW3 ተብሎ በሚጠራው ማጠራቀሚያ እና ግፊት መስጫ ጣቢያ የሚገባው ውሃ መሃል አዲስ አበባ ለመድረስ ከ10 በላይ የቅብብሎሽ ሂደቶችን ያልፋል፤ ይህም ሂደት የውሃ ስርጭት ሂደቱን ውስብስብ ያደርገዋል፡፡

ይህ ብታውቁት ብለን ያሰፈርነው መረጃ የውሃ ስርጭቱን እንጂ የምርት ሂደቱን የሚያሳይ አይደለም፡፡ የምርት ሂደቱን በተመለከተ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን፡፡