የለሚ ኩራ ቅርንጫፍ ጽህፍት ቤት ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ስሙ ጭላ ፈታ አካባቢ 500 አርሶ አደሮችን የንፁህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ አድርጓል።1.6 k.m ርዝመት ያለው መስመር ተዘርግቶ ከአካባቢው ነዋሪው በተዋጣ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ፕሮጀክቱ ተገንብቶ ለአገልግሎት በቅቷል።በፕሮጀክት ርክክቡ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የቦሌ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ተስፋዬ ሰይፉ እንደገለጹት አከባቢው በከተማ አስተዳደር ክልል ውስጥ ቢሆንም ከመሰረተ ልማት አቅርቦት የተገለለ እንደነበረ አስታውሰው በውና ፍሳሽ ባለስልጣን ለተሰራው ስራ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡ በሌሎች መሰረተ ልማት አቅራቢዎችም ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡በባለስልጣኑ የለሚ ኩራ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ሙልጌታ አስፋው በበኩላቸው በከተማ ውስጥ የሚገኙ አርሶአደሮችን በቦኖ ውሃ እና በመስመር የንጹኅ ውሃ ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 11 ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አማን አምዳ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመልክም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሆ ገልጸው ባለስልጣኑ ቅድሚያውን ወስዶ ላደረገላቸው ቀና ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ሌሎች የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ህብረተሰቡ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡