ጣፎ አደባባይ አካባቢ የሚገኝ የየካ አባዶ ሳይት የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ መስመር ባልተገባ አጠቃቀም ምክኒያት ተዘግቶ ፍሳሹ እየገነፈለ ለነዋሪዉ ፈተና ፤ለአላፊ አግዳሚው ለመጥፎ ጠረን ዳርጎ ሰነባብቷል፡፡ፍሳሹም በማንሆል ገንፍሎ መንገድ ላይ በመፍሰሱ ምክኒንያት ነዋሪዎች ቅሬታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ከስፍራው የፍሳሽ ቆሻሻ ሰብስቦ ወደ ኮተቤ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ የሚያጓጉዘው ከፍተኛ የፍሳሽ መስመር መዘጋትን ተከትሎ ችግሩን ለመቅረፍ በተደጋሚ የመስመር ጽዳት ቢያደርግም ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ አልተቻለም ነበር፡፡ባለስልጣኑ የችግሩን ግዝፈት በመረዳት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ክፍተኛ ርብርብ ማድረጉን የፍሳሽ ከፍተኛ መስመር ዝርጋታ ጥገና እና መረብ ቁጥጥር ንዑስ የስራ ሂደት መሪ አቶ አቦነህ ባዩ ተናግረዋል፡፡የፍሳሽ መስመሩ የተዘረጋበት ጥልቀት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ መስመሩን ፈልጎ ችግሩን ለመለየት እስከ 14 ሜትር ጥልቅት መቆፈር፣ በዚሁ ጥልቀት ላይ ባልታወቀ ምክንያት የፍሳሽ መስመሩ ከ6 ሜትር በላይ ተሰብሮ መገኘቱን ብሎም በአካባቢው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሀይል ተሸካሚ ምሶሶ መኖሩ ስራውን ውስብስብ እንዳደረገው አቶ አቦነህ አብራርተዋል፡፡የባለስልጣኑ የፍሳሽ ዘርፉ ሰራተኞች ቀን ከሌት በመስራት ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ የጥገና ስራው ሙሉ በሙሉ ማከናወን ተችሏል፡፡ተንዶ የነበረውን 12 ሜትር ርዝመት በ4 ሜትር ከፍታ የፍሳሽ መስመር የድጋፍ ግንብ እንደገና በመገንባት የፍሳሽ መስመሩ ያለችግር ተግባሩን እንዲያከናውን ተደርጎ የአካባቢው ችግር ተፈቷል፡፡አቶ አቦነህ የአካቢው ነዋሪዎች በፍሳሽ መስመር ውስጥ መግባት የሌለባቸው ጠጣር ነገሮችን በመጨመር ከፍተኛ ችግር መፍጠራቸውን በመረዳት ለመሰረተ ልማቱ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላፈዋል፡፡