በቀን 100,000 ሜትር ኪዩብ የማጣራ አቅም ያለው የቃሊቲ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ፕሮጀክት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ቅዳሜ ሰኔ 30/2010 ተመርቆ ስራ ጀምሯል፡፡

ከዓለም ባንክ በተገኘ 100 ሚሊዮን ዶላር ብድር እና ከመንግስት በተመደበ 759 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ፕሮጀክት ግንባታው በ2008 አጋማሽ ላይ ተጀምሮ በተቀመጠለት ጊዜ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የ7 ክፍለ ከተሞችን ፍሳሽ በመስመር ተቀብሎ በማስተናገድ ከ1.5 ሚሊዮን ህዝብ በላይ የከተማዋን ነዋሪ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

በምረቃው ስነ – ስርዓት ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያው ፕሮጀክት ግንባታ የወቅቱን ቴክኖሎጂ በመጠቀሙ ለከተማዋ አዲስ ጅምር መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፣ ሁላችንም እኩል የምንኖርባት፤ ሁላችንም እኩል የምንገለገልባት አዲስ አበባን መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ሌሎች መሰል ፕሮጀክቶችን በመገንባት መዲናዋን ወደፊት ልናራምዳት ይገባል ብለዋል፡፡

ይኼን እውነት ለማድረግም ባለፉት ዓመታት በባለስልጣኑ የተከናወኑ ተግባራት ጥሩ ርምጃዎች ቢሆኑም ከከተማዋ ዕድገትና ከህብረተሰቡ ፍላጎት አኳያ እፍኝ የሚሞሉ ስላልሆነ ያን የሚለውጥ እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርብናል” ሲሉ አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በበኩላቸው “በባለፉት አምስት ዓመታት የከተማዋን ፍሳሽ አወጋገድ ዘመናዊ ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ለውጦች መምጣታቸውን ገልፀው ከከተማዋ የሚወጡ ፍሳሽ ቆሻሻዎችን በተማከለ

እና ባልተማከለ መልኩ በተሸከርካሪ ብሎም በመስመር ሰብስቦ በማስወገድ አስተዳደሩ ረጅም ርቀት መጓዙን ጠቁመዋል፡፡

በተማከለ እና ባልተማከለ የማጣሪያ ዘዴ ፍሳሽ እንዲወገድ የማድረግ ተግባራቱን አጠናክሮ በማስቀጠል በ2006 ከነበረበት በቀን 10,000 ሜትር ኪዩብ ከ146,450 ሜትር ኪዩብ በላይ ማሳደግ መቻሉን ጨምረው አስረድተዋል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አወቀ ኃ/ማሪያም (ኢንጂነርና አርክቴክት) ፕሮጀክቱ ከዚህ በፊት ከተገነቡት ሁሉ ልዩ የሚያደርገውን አስመልክተው ሲናገሩ “በዓለም ያለን ወቅታዊና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የተጠቀመ ሲሆን፣ በትልቅነቱም በም/አፍሪካ የመጀመሪያው ነው” ብለዋል፡፡ በግንባተው ላይ በመሳተፍ አስተዋፅኦ ያበረከቱ አካላትን አመስግነው “ወደፊት ሙያዊ ድጋፋችሁ እንዳይለየን” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡