ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ የለገዳዲ ግድብ ማስተንፈሻ በሮች ጥገና ፕሮጀክት ፣ የተፋሰስ ልማት እና የማሰልጠኛ ተቋም ስራዎች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ በስፋራው ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡

አቶ ጃንጥራር በዚሁ ወቅት ከባህዳር የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት የመስክ ላይ የአመራርነት ስልጠና (FLL) ለወሰዱ ሰራተኞችም የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል፡፡

በግድቡ አካባቢ የተሰራው የተፋሰስ ልማት ስራ በጥሩ ደረጃ እንደሚገኝ ገልጸው ፤ በዙሪያ የሚታየው ወረራ ግን ትልቅ ትኩረትና ስራ የሚፈልግ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የለገዳዲ ግድብ ማስተንፈሻ በሮች እና ተያያዥ የጥገና ፕሮጀክቶቹም ያሉበትን ሁኔታ የጎበኙት ም/ከንቲባው ስራው እስኪጠናቀቅ ድረስ ከፍተኛ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ም/ከንቲባው ከባህዳር ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት የመጡ ሰራተኞችን የምስክር ወረቀት በሰጡበት ወቅት እዳሉት ውሃና ፍሳሽ እንደ ከተማ ትኩረት የሚሰጠው ተቋም መሆኑን ገልጸው፤ አሁን እየሰጠ ያለው ስልጠና ደግሞ የተቋሙን አገልግሎት ከፍ የሚያደርግ እንደመሆኑ ሰልጣኞችም በስልጠና ያገኙትን ወደ ተግባር በመቀየር ለተቋማዊ ለውጥ መረባረብ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

እንዲህ አይነት ስልጠና በውሃ ላይ የሚሰሩ ተቋማትን ትስስር የሚያጠናክርና አንዱ ከአንዱ ልምድ የሚቀስምበት በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል፡፡

ስልጠናው የተሰጠው ቪቴንስ ኢቪደስ ኢንተርናሽናል ከተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ነው፡፡

ባለስልጣኑ በራሱ ሰራተኞች የጀመረውን ይህን ስልጠና በሀገር ውስጥ ፡-ለኦሮሚያ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ እና ለባህርዳር ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት፣ ከሀገር ውጪ ደግሞ ለኬኒያ፣ ለሞዛምቢክ የውሃ ተቋማት ያሰለጠነ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በህንድ ሀገር ለጋና የውሃ ተቋም ሰራተኞች እየሰጠ ይገኛል፡፡