ባለስልጣኑ የተፈራረመው ከጃፓን ዓለም አቀፍ ድርጅት (JICA) ጋር ሲሆን ስምምነቱም በውሃ ብክነትን መቀነስ እና ስርጭቱን ማስተካከል ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ከ51ሺኅ በላይ ደንበኞችን ያቀፈ ሲሆን በንፋስ ስልክ እና መካኒሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ላይ የሚተገበር ነው ፡፡በአሁኑ ሰዓትም ከተጠቀሱት አካቢዎች መረጃ በመሰብሰብ እና የተመረጡት ቅርንጫፎች ወቅታዊ የሆነ መሰረተ ልማቶችን ካርታ ላይ የማስፈር ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ በባለሥልጣኑ ገቢ የማይሰበሰብበት ውሃ ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ሃብታሙ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ ባለሙያው አክለውም በቀጣይም ድርጅቱ በተመረጡት ቅርንጫፎች ከተሰራጨው ውሃ ምን ያህሉ ጥቅም ላይ ይውላል? ምንስ ያህሉ ይባክናል? የት አካባቢ? የሚለውን በመለየት አስፈላጊውን የስርጭት ማስተካከያ እንደሚያደርግ አብራርተዋል፡፡ ስራው የሚባክን ውሃ ከመቀነስ ባለፈ ለስርጭት ባለሙያዎች ክህሎትን ለማዳበር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽ ይኖረዋል ፡፡ ፕሮጀክቱ ለአራት አመት የሚቆያ ሲሆን ለስራ የሚያስፈልጉ ማንኛውም ግብዓቶች በጃፓን ዓለም አቀፍ ድርጅት (JICA) የሚሸፈኑ ይሆናል ፡፡