ባለሥልጣኑ የማህበራዊ አገልግሎቱን ለመወጣት ላለፉት ስምንት ዓመታት ለታዳጊዎች እና ህጻናት የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ድጋፉን የሚደረገውም ከሰራተኞች በሚሰበሰብ የገንዘብ መዋጮ ሲሆን በየውሩ ለእያንዳንዳቸው 600 ብር ይደርሳቸዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን በዋና ዋና በአላት ወቅት ለበአሉ መዋያ የሚሆናቸው ስድስት መቶ ብር በነብስ ወከፍ በተጨማሪነት በስጦታ መልክ ለቤተሰቦቻቸው ወይም ለአሳጊዎቻቸው ይሰጣል፡፡

በነገው እለት ለሚከበረው የገና በዓል የስጦታ ሥነ-ስረዓት ላይ ተገኙት የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘሪሁን አባተ ለታዳጊዎችና ቤተሰቦቻቸው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ስራ አስኪያጁ አክለውም ማኅበራዊ ሃላፊነትን መወጣት እንደተቋምም ሆነ እንደግለሰብ ተገቢ መሆኑን አስታውሰው፤ ተቋሙ ይህንን ድጋፍ በማጠናር ለታዳጊዎች ብቻ ሳይሆን ሌሎች አካላትን በማካተት የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የተቋሙ ሰራተኛ ማህበርም በዚህ ተግባር ላይ ከፍተኛውን ድርሻ በመውሰድ እንደሚሰራ የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ወረቁ አንዷለም በዚሁ ወቅት አስረድተዋል ፡፡

ባለስልጣኑ ከሚደግፋቸው ታዳጊዎች መካከል ባለፈው ዓመት አንድ ወጣት የኮሌጅ ትምህርቱን በማጠናቀቁ እርዳታው እንዲቋረጥ ከምስጋና ጋር ጠይቆ የተሰናበተ ሲሆን፤

የእርሱን አርዓያነት የተከተሉ ሁለት ሴት ታዳጊዎች በደ/ታቦር ዩኒቨርሲቲ እና አንድ ወንድ እንዲሁም ሁለት ሴቶች ደግሞ በግል ኮሌጅ ትምህርታቸውን እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡