አዲስ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የካይዘን ፍልስፍናን መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ ህብረተሰቡን ለማርካት እና ለሰራተኛው ምቹ የስራ ቦታ ለመፍጠር እንዲሁም ስር ነቀል የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት እየተጠቀመበት እንደሆነ ገለጸ፡፡ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የካይዘን ፍልስፍና ተግባራዊ በማድረጉ የአገልግለት አሰጣጡን ከፍ ማድረግ መቻሉ ተጠቁመሟል፡፡

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ወርቁ ገዳ እንደገለጹት  የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የለውጥ መሳሪያዎችን የአሰራር ሲስተም አድርጎ መጠቀም ለአንድ ተቋም ውጤታማነት ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ከእነዚህ የለውጥ መሳሪያዎች አንዱ ደግሞ በተወሰኑ ተቋማት ላይ እየተተገበረ ያለው የ“ካይዘን” ፍልስፍና ነው፡፡ የካይዘን ፍልስፍናን የተመለከተ ስልጠና ለሁሉም የቅርንጫፉ አመራሮች እና ፈጻሚዎች  ተሰጥቶ ወደ ትግበራው ተገብቷል፡፡

እነደ አቶ ወርቁ ማብራሪያ ትግበራውን ተከትሎ በሂደት ለውጥ መታየት ሲጀምር በሰራተኛው መካከል ጤናማ የፉክክር መንፈስ በመፈጠሩ በራስ ተነሳሽነት አረንጓዴ ልማት የማስፋፋት፣ የተለያዩ ግንባታዎችን የማካሄድና አካባቢን የማስዋብ ብሎም ቢሮዎችን የማደራጀት ስራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም በውጪ ባለሙያ ቢሰራ ሊወጣ የሚችለው በሚሊየን የሚቆጠር ብር ማስቀረት ተችሏል፡፡ ስፍራዎችን የማስዋብ ስራ በመሰራቱም ፈፃሚዎች በእረፍት ሠዓታቸው ውጪ መውጣት ሳያስፈልጋቸው ባሉበት አካባቢ እንዲያሳልፉ አድርጓል፡፡

ነባርና አዳዲስ የመዝገብ ቤት ካቢኔቶች በክፍለ ከተማ፣ በወረዳ እንዲሁም በቁጥር ተለይቶ በካይዘን ቻርት አመዘጋገብ ስርዓት በመስፈራቸው ሰነዶችን ለማግኘት ቀላል ከማድረጉም በላይ የሰዓቱን ስታንዳርድ ማሻሻል ተችሏል፡፡