በብዙ ውጣ ወረድ እና ውስብስብ ሂደት ተመርቶ ወደ እያንዳንዳችን ቤት፣ተቋማት እና ድርጅቶች የሚሰራጨው የመዲናዋ የውሃ ጥራት የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) መስፈርትን በማሟላት ነው፡፡

የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን ምንም እንኳን የዓለም ጤና ድርጅት የሚያዘው  ከአዲስ አበባ ህዝብ ቁጥር አንጻር በቀን 18 ናሙናዎች እንዲወሰድ ቢሆንም በየእለቱ ከማጠራቀሚያ ፣መግፊያ ጣቢያዎች እና ግለሰቦች ቤት ሰላሳ(30) ናሙና በመውሰድ እና በላብራቶሪ በመፈተሽ  የክትትል እና ቁጥጥር ስራ ያከናውናል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ይህን አኃዝ ያስቀምጥ እንጂ የከተማችን ስፋት እና በየጊዜው ከሚከናወነው  የመንገድ ፣ የቴሌ፣ በአካባቢ ብሎም መልሶ ማልማት ግንባታዎች ምክንያት የውሃ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ስለሚያስከትሉ አስተማማኝ የናሙና መጠን ለመውሰድ ሲባል ቁጥሩን ከፍ ማድረግ እንዳስፈለገ የባስልጣኑ የየተፋሰስ አስተዳደር እና የውሃ ጥራት ቁጥጥር ንዑስ የስራ ሂደት መሪ አቶ ዘለቀ ተፈሪ  አስረድተዋል፡፡

በባለስልጣኑ የፊዚኮ ኬሚካል፣ ማይክሮ ባዮሎጂካል፣ የባዮሎጂካል፣ በመጠጥ ውሃው ውስጥ ያለውን ትርፍ ክሎሪን መጠን  የመከታተል ስራ፣ የውሃ ማጣሪያ እና ማከሚያ ኬሚካል ጥራት ምርመራ እና ለማጣሪያ እና ለማከሚያ የምንጠቀምበት ኬሚካል መጠን የመወሰን ስራ ይሰራል፡፡

በውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎች ውሃውን ለማጣራት እና ለማከም የሚጠቀሙባቸው ኬሚካሎች ጥራት እና መጠን አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ የመወሰን ስራ እና በማጣሪያ ጣቢያው የሚጣራው ንጹህ የመጠጥ ውሃ በሚጠበቅበት የጥራት ደረጃ መጣራቱም በየእለቱ ይከናወናል፡፡

የውሃ ጥራት ክትትልና ቁጥጥር ስራውም ከውሃ መገኛው ጀምሮ  እስከ ነዋሪው  ቧንቧ ድረስ የሚከናወን ሲሆን የውሃውን ጥራት ለማስጠበቅም  የውሃ መገኛ አካባቢው ለብክለት ተጋላጭ አለመሆናቸውን  ማረጋገጥንም  ይጨምራል፡፡

የውሃ መገኛ አካባቢዎች ስነ ምህዳር ለመጠበቅ እና አፈር እንዳይሸረሸር ለማድረግም በየአካባቢው የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ከመስራት ጎን ለጎን የአካባቢው አርሶ አደሮች  ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ እንዲጠቀሙ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ይሰራል፡፡