የስራ አስኪያጅ መልእክት

ጤና ይስጥልን ! በከፍተኛ ፍጥነት  እያደገ  የሚገኘውን  የከተማችንንና የነዋሪዎቿን  የመሠረተ ልማት ፍላጎትን ከአቅርቦቱ ር የማጣጣም ሁለንተናዊ ጥረቶች አካል የሆኑ አምስት ሚሊዩን በላይ ነዋሪዎች እንደሚኖሩባት የሚገመተው  ከተማችን አዲስ አበባን ለኑሮ ለስራና ለጉብኝት ምቹ ማድረግን በማሰብ መንግስት ሠፊ ትኩረትን በመስጠት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡  በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ  መንግስት  ከአስር ቢሊን ብር በላይ የሆነ በጀት በመመደብ ለውሀ ፕሮጄክቶች ከፍተኛ አጽንኦት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡በዚህ በጀት አመትም አምስት ቢሊዮን ብር በመመደብ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ፡፡  ከዚሁ በተጓዳኝም የፍሻስ ማጣሪያ ጣቢያዎች ግንባታንና የፍሳሽ መረብ / እውታሮችን ማጎልበትና  የማስፋፊያ ሥራዎችንም አጠናቋል፡፡  እንዲሁም ግልጋሎቱን  የማዘመን ጥረቱ አካል የሆኑና አገልግሎቱን ለማሳለጥ ያስቻሉ የፍሳሽ ማንሻ ተሸከርካሪዎች ግዢዎችንም  ያካተቱ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውኗል፡፡  

ውድ የከተማችን ነዋሪዎች ÷ባለስልጣኑ በተለይም በውሀ አቅርቦት የሥራ ዘርፍ ረገድ ÷  የከተማችንን የውሀ ፍላጎት አቅርቦት ማሟሏትን ታሳቢ ያደረጉ ፣ የገፀ- ምድርና የከርሰ ምድር የውሀ ምንጮችን  መሰረት ያደረጉ አማራጮችን ያካተቱ ፣ የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን ከሚመለከታቸው የመንግስትና አጋር ባለድርሻ አካላት ጋ በቅንጅት  አዘጋጅቶ በትግበራ  ሂደት ውስጥ እንደሚገኝ በአክብሮት ለማሳወቅ  ይወዳል፡፡ በ2010 በጀት አመት  አምስት መቶ ሃያ አምስት ሽህ ምትር ኪዩብ የነበረውን በቀን ዉሃ የማምረት አቅም ከፍ ለማድረግ በዚህ አመት ጅምር ስራዎችን በማጠናቀቅ እና በመዲናዋ ኪስ ቦታች ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን በማጎልበት  በድምሩም በአሁኑ ወቅት  የከተማችንን ዕለታዊ የውሀ አቅርቦትን ወደ አምስት መቶ ሰባ አራት  ሺ ሜትር ኪዩብ / በዕለት ከፍ ለማድረግ ተችሏል፡፡  ይሁንና የወቅቱ የአዲስ አበባችን ዕለታዊ የውሀ ፍላጎት ዘጠኝ መቶ ሰላሳ ሺ ሜትር ኪዩብ በመሆኑ ፤ ይኽንኑ  ክፍተት ለመሙላትና አቅርቦትንና ፍላጎትን ለማጣጣም ይቻል ዘንድ  በዋነኛነት ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ብዙ እንደሚጠበቅ  አበክረን የምንገነዘበው  ሀቅ ነው፡፡

አጭር የጊዜ ወሰን ዕቅድ ማዕቀፍ ውስጥ ÷ የከተማዋን ዕድገት ተከትሎ የተከሰተውን ከፍተኛ የሆነ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ፍላጎት ማርካት እንዲቻል የተለያዩ ጊዜያዊ እርምጃዎች በመተግበር ላይ  ይገኛሉ ፡፡ ከእነዚህም መካከል ቀዳሚዎቹ ÷  በተቋሙ ውሃ ስርጭት ፍትሃዊ ያለመሆን  ከፍተኛ ችግር የሚታይባቸው አካባቢዎችን  የመለየት ፤ የስርጭት ችግሩ መንስኤዎችንና ሊፈቱ የሚችሉባቸውን  አግባቦች  ተቋሙ በተውጣጡ ባለሙያዎች  የማጥናት ተግባራት ተከናውነዋል ፡፡ በውጤቱም የውሃ ስርጭት ችግ መንስኤዎችን የመለየት  ፣ የውሃ እጥረት በስፋት በሚከሰትባቸው የከተማዋ ክፍሎች/ አካባቢዎች የሚያስፈልገው የውሃ መጠን እና የአቅርቦት አማራጮች  በዝርዝር ተጠንተውና ታውቀው በእቅድ እንዲያዙ ተደርገዋል፡፡ ውሃ በፈረቃ የመስጠቱና የማዳረሱ  ተግባር እንደ አንድ አማራጭ በጊዜያዊነት እየተወሰደ ካሉ መፍትሔዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የአቅርቦት ዕጥረቱ እንዳለ ሆኖ ፤ ሚዛናዊ የውሀ ሥርጭት እንዲኖር  የሚያስችሉ (ከውሃ ምርት እጥረት ውጪ ያሉ መንስኤዎችና አስተዋጽኦ ካላቸው ጉዳዩች ባሻገር  ያሉ ጉዳዩችን በዝርዝር የመለየትም ተግባር እንዲሁ ተከናውኗል፡፡

ለውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ዘርፍ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረትም÷ በተለይም ለተጓተቱ ፕሬጄክቶች የቅድሚያ አጽንኦት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም መካከል  ÷   በቀን  ስድሳ ስምንት ሺ ሜትር ኪዩብ / ዕለታዊ  የማምረት አቅም ያለው ሳውዝ አያት ኖርዝ ፈንታ ፕሮጀክት  እንዲሁም በቀን ሰማንያ ስድስት ሺ ሜትር ኪዩብ/ ዕለታዊ  የማምረት አቅም ያለው የለገዳዲ ሁለተኛው ምዕራፍ  የጥልቅ ጉድጓድ ፕሮጀክቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተጨማሪም የሰሜን አዲስ አበባን በርካታ የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ÷ የገርቢ ግድብ ፕሮጀክት አጋጥሞት የነበረውን የወሰን ማስከበር ችግር የከተማችን ም/ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር በመነጋገር ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ ፈር የማስያዝ ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል የከተማዋን የፍሳሽ ማስወገድ ስርዓት ለማዘመን እና የመዲናችንን ፍሳሽ በመስመር የማንሳት ሽፋን አሁን ካለበት ዝቅተኛ ደረጃ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በመስራት ላይ እንገኛለን ፡፡ ለዚህም በፍሳሽ ዘርፍ ዋና ዋና ግቦችን ለማስቀመጥ ይረዳ ዘንድ በከተማዋ ውስጥ የሚኖረውን የህዝብ ብዛት፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ፍሳሽ አገልግሎት ፍላጎት መጠን ጥናት ተከናውኗል  ፡፡ በመሆኑም የውሃ አቅርቦቱን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራው ሁሉ ፍሳሽ አሰባሰብና አጣርቶ የማስወገድ ሽፋን የሚያሳድጉ  ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ማስፋፋት ፣  የፍሳሽ መስመር ዝርጋታና የፍሳሽ ደንበኞች መስመርን የመቀጠል  ስራ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠውና ሊሠራ የሚገባ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል ይህንንም ተቋማችን በትኩረት እየሰራበት ነው፡፡

ባለስልጣኑ በውሃ ልማት እና ስርጭት ብሎም የፍሳሽ አወጋገድ ላይ  እንደሚሰራ ሁሉ በተፋሰስ ልማት ስራም በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡

ባጠቃላይ የከተማችንን ህብረተሰብ ፍላጎት ለማርካት አገልግሎቱን ዘመናዊ እና ተደራሽ ለማድረግ ብዙ ስራ እንደሚጠበቅብን እሙን ነው፡፡ በመሆኑም ያልሰራናቸው ብዙ የቤት ስራዎች እንዳሉ ግንዛቤ በመውሰድ ከተማ አስተዳደሩ የሰጠንን እና ህዝባችንን የሚጠብቅብንን ሀላፊነት ለመወጣት ቀን ከሌት የመስራት ቁርጠንነታችን እየገለጽን ፣ ከከተማችን ነዋሪዎችና ከባለድርሻ  አካላት ጋ እጅ ለእጅ ተያይዘን በቅንጅት በአብሮነት ለመፍትሔ የእንስራ ጥሪያችንን ለማቅረብ እንወዳለን!