የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የደንበኞች ፎረም መመሪያ
መ/ቤቱ የንፁህ ውሃ አቅርቦትና ፍሳሽ ማስወገድ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በ8ቱም ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ባለፉት ስድስት ዓመታት የደንበኞች ፎረም ማካሄዱ ለአገልግሎት አሰጣጡ መሻሻል ገንቢ የሆኑ ግብዓቶች መገኛ መድረክ ቢሆንም የአደረጃጀቱ ሁኔታና ተግባሩ ባለመወሰኑ ፣ምንም አይነት ማትጊያ ባለመኖሩ፣ ወጥ በሆነ መልኩ ሊያሰራ በሚችል መመሪያም ባለመደገፉ ጭምር ውጤቱ ከቅርንጫፍ ቅርንጫፍ የተለያየ እንዲሆንና የተፈለገውን ግብ እንዳይመታ አድርጎታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ሲል በነበረው ፎረም የፎረም አባላት ዕቅድ እና ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ከመወያየት እና ጥቆማ ከመስጠት ባለፈ የተቋሙን ተልዕኮ በመጋራት ማህበረሰቡ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ፎረሙ ያበረከተው ግብዓት ባለመኖሩና የህዝቡን በልማት ላይ ያለውን ተሳትፎ እና ወሳኝ ሚና ሳይጫወት ቀርቷል፡፡
በመሆኑም ፎረሞቹ ተመሳሳይነት ባለው ሁኔታ በሁሉም ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ለማካሄድ፣የደንበኞቹ ፎረም ምክክርና እንቅስቃሴ የተሻለ ውጤታማ ለማድረግ፣በሀገር አቀፍ ደረጃ መልካም ተሞክሮ እንዲሆን ለማድረግ፣ ፎረሙ ጠንካራ የህዝብ ግንኙነት እና የንቅናቄ ሥራዎችን ማሳኪያ ለማድረግና በአጠቃላይ ፎረሞቹ የተቋቋሙበት አላማን ከግብ ለማድረስ ሊያሰራና ሊያግዝ በሚያስችል መልኩ መመሪያውን እንደገና ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህ የደንበኞች ፎረም መቋቋሚያ መመሪያ ወጥቷል፡፡
ክፍል አንድ
ጠቅላላ
አንቀፅ 1
አውጪው ባለስልጣን
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 10/1986 አንቀፅ 20(6) በተሠጠው ሥልጣን መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡
አንቀፅ 2
አጭር ርዕስ
ይህ መመሪያ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የደንበኞች ፎረም እንደገና ማቋቋሚያ መመሪያ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
አንቀፅ 3
ትርጓሜ
የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ መመሪያ ውስጥ ያሉ ቃላቶች የሚከተለውን ትርጉም ይይዛሉ ፡-
- የቅርንጫፍ የነዋሪዎች ፎረም ማለት የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ገንቢ የሆነ አስተያየት፣ ጥቆማና ሃሳቦች ለማቅረብና ህብረተሰቡ በልማት ላይ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ ውይይት ለማድረግ ከህብረተሰቡና ከልዩ ልዩ አደረጃጀቶች አካላት የተወጣጡ የመ/ቤቱ ደንበኞች ከመ/ቤቱ ጋር የጋራ ምክክር እንዲያደርጉ በቅርንጫፍና በከተማ ደረጃ የተቋቋመ አደረጃጀት ማለት ነው፡፡ እንደ የቅርንጫፉ ተጨባጭ ሁኔታም ከ250-300 አባላት ይኖሩታል፡፡ የእያንዳንዱ ቅርንጫፍ የነዋሪዎች ፎረም በሦስት ወር አንድ ፣ በዓመት አራት የግንኙነት ጊዜያት ይኖሩታል፡፡
- የከተማ የነዋሪዎች ፎረም ማለት ከእያንዳንዱ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሀምሳ፣ ሀምሳ አባላት ተዋጽዖ ተመሥርቶ በጋራ ውይይት የሚደረግበት አደረጃጀት ሲሆን፣ ከ400 እስከ 500 አባላት ይኖሩታል፡፡
- መ/ቤት ማለት የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ማለት ነው፡፡
- ቅርንጫፍ ማለት መ/ቤቱ ዓላማዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያመቸው መልኩ በሥልጣኑና በአገልግሎት ክልል ውስጥ እንደአስፈላጊነቱ ያቋቋመው ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ነው፡፡
- “የነዋሪዎች ፎረም የበላይ ኮሚቴ” ማለት ከፎረሙ ጠቅላላ ጉባዔ በሚመረጡ 10 አባላት የሚዋቀር ሆኖ በየ15 ቀኑ እየተገናኘ የሚወያይ አደረጃጀት ነው፡፡
- “የቅርንጫፍ ጽ/ቤት የነዋሪዎች ንዑስ ፎረም” ማለት ከየቅርንጫፉ የነዋሪዎች ፎረም መካከል በሚመረጡ 50 አባላት የሚዋቀርና በየወሩ እየተገናኘ ከየቅርንጫፉ የውሃና የፍሳሽ አገልግሎቶች አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ሥራዎች፣ ችግሮችና መሰል ጉዳዮች ላይ የሚወያይ አደረጃጀት ነው፡፡
- “አገልግሎት” ማለት በመ/ቤቱ የሚሠጠው የንፁህ ውሃ አቅርቦት፣ፍሳሽ ማስወገድና ከነዚሁ ጋር ተያይዘው የሚሠሩ ሥራዎችን በሙሉ ይጨምራል፡፡
አንቀፅ 4
የመመሪያው ተፈፃሚነት
ይህ መመሪያ በመ/ቤቱ የፎረም አደረጃጀትና አሠራር ሲባል በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡ አንቀፅ 5
ስለደንበኞች ፎረም መቋቋም
የመ/ቤቱ የደንበኞች ፎረም በየቅርንጫፉ እና የከተማ ፎረም በማዕከል በዚህ መመሪያ መሠረት እንደገና ተቋቁሟል፡፡
ክፍል ሁለት
የፎረም አደረጃጀት፣ ተጠሪነት፣ ሥልጣንና ተግባር
አንቀፅ 6
የፎረም አደረጃጀት እና ተጠሪነት
የመ/ቤቱ የደንበኞች ፎረም በየቅርጫፍ እና የከተማ ፎረም በማዕከል ደረጃ የሚከተለው አደረጃት ይኖረዋል፡፡
- በእያንዳንዱ ቅርንጫፍ ሁሉንም የቅርንጫፉ የውሃና ፍሳሽ ተጠቃሚዎች ፣ የአከባቢ ተወካዬች የሚወክሉ ከ300 እስከ 350 የሚሆኑ የፎረም አባላት ይኖሩታል፡፡ ዝርዝሩ በሰንጠረዥ የተመለከተው ይሆናል፡፡
- የከተማ ፎረም አባላት በየጊዜው በሚደረገው የቅርንጫፎች መደበኛ ስብሰባ ወቅት በአባላት የሚመረጡት ከ 400 እስከ 300 የሚሆኑ አባላት ናቸው፡፡ከእያንዳንዱ ቅርንጫፎች የሚወከሉ አባላት ቁጥር ከ50 ማነስ የለበትም፡፡ ዝርዝሩ በሰንጠረዥ የተመለከተው ይሆናል፡፡
- የደንበኞች ፎረም አባላት በየአንዳንዱ የመ/ቤቱ ቅርንጫፍ ከወረዳና ክ/ከተማ አስተዳደር ስራ አስፈፃሚ ፅ/ቤቶች፣ ከወረዳና ክፍለ ከተማ ምክር ቤት፣ ከዕድሮች፣ ከንግድ ድርጅቶች፣ ከወጣትና ሴት ማህበር፣ከፖሊስና ከደንብ አስከባሪዎች፣ ከነዋሪዎች ፎረም፣ከወረዳና ከክፍለ ከተማ የኮሚኒኬሽን ባለሙያ፣ ከሴቶችና ወጣቶች ሊግ፣ ከክ/ከተማ እና ወረዳ ጤና ፅ/ቤት፤ ከክፍለከተማ እና ወረዳ ስራ አስኪያጅና ከመሬት ልማት ማኔጅመንት ፅ/ቤት ከተለያዩ የማህበረሰቡ አደረጃጀትና ነዋሪዎች፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከአከበቢ ልማት ኮሚቴ፣ ከቅርንጫፉ የውሃና ፍሳሽ ፅ/ቤት የሚመለከታቸው ኃላፊዎች፣ የውሃ ቴክኒሺያኖች፣ የፍሳሽ ክለርኮች (ቡድን መሪዎች) ሙያተኞች የተወጣጡ ሲሆን የከተማ ፎረም ከየቅርንጫፉ ከሚመጡት አባላት በተጨማሪ የመዓከሉ እና የቅርንጫፍ የውሃና ፍሳሽ ፅ/ቤት የሚመለከታቸው ኃላፊዎችና ሙያተኞች ፣ የከተማ ተወካዮች ፣ የቢሮ ኃላፊዎች ፣የክ/ከተማ ስራ አስፈፃሚዎችና አስፈላጊ የሆኑ አካላት ድምር ነው፡፡
- የፎረም አባላት ያገልግሎት ግዜ 1 ዓመት ሲሆን፤አስፈላጊ ከሆነ ለተጨማሪ 1 ዓመት ሊራዘም ይችላል፡፡
- የቅርንጫፍ የፎረም ሰብሳቢ የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅና የክ/ከተማው ስራ አስፈፃሚዎች በጋራ፤ምክትል ሰብሳቢዎች ከተሣታፊው የሚመረጡ ሁለት ጠንካራ ሰዎች ሲሆኑ ፀሀፊ የቅርንጫፉ የውሃና ፍሳሽ ዘርፍ ይሆናሉ፡፡
- የከተማ ፎረም ሰብሳቢ ከከተማው የበላይ ኃላፊዎች ጋር የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ፤ ምክትልና ፀሀፊውም ከባለስልጣኑ ማኔጅመንት አባላት መካካል ይሰየማል፡፡
- እያንዳንዱ ቅርንጫፍ በየወሩ እየተገናኙ የሚመክሩና ስራን የሚገመግሙ ከጠቅላላ ጉባኤተኞች የሚመረጡ “የጠቅላላ ጉባኤ አባላት” በአጠቃላይ ላይ ፎረሙ እና በፎረሙ የበላይ ኮሚቴ መሀል ላይ ሆኖ የሚሰራ 50 አባላት ይኖሩታል፡፡ ከመካከላቸውም የፎረሙን የበላይ ኮሚቴ ይሰይማሉ፡፡
- የደንበኞች ፎረሙ በየቅርንጫፉ ከነዋሪዎች ፎረም፣ከቅርንጫፍ የፍሳሽና የውሃ ንዑስ ሥራ ሂደት ከክ/ከተማ ም/ቤቶች ፣ ከደንብ ማስከበር፣ ከፖሊስ እና ከቀጠና ልማት አስተባባሪዎች እንዲሁም እንዳስፈላጊነቱ ከቅርንጫፉ የፎረም አባላት መካከል በድምሩ 15 የሚደርሱ ሰዎች ያሉት የበላይ ኮሚቴ ይኖረዋል፡፡
- የቅ/ጽ/ቤት ስራ አስኪጅ፣ የውሃ እና የፍሳሽ ደንበኛ አገልግሎት ን/የ/ሂደት መሪዎች፣ የውሃ እና የፍሳሽ ሲኒየር ቴክኒሺያኖች፣ የፍሳሽ ስምሪት አስተባባሪ፣ የደንበኞች አቤቱታ ተቀባይ እንዲሁም የቆጣሪ ንባብ እና የቁፋሮ ማህበራት ተወካዮች የቅርንጫፍ ጽ/ቤት የደንበኞች ፎረም አባላት ይሆናሉ፡፡
- ቃለ-ጉባኤ መያዝ ሥራው የሚሠራው በመ/ቤቱ የኮሚኒኬሽን ጉዳዬች ደ/የሥ/ሂደት በሚመደብ ባለሙያ እና ቅርንጫፉ በሚመድበው ሌላ ሰው ይሆናል፡፡
- የቅርንጫፍም ሆነ የከተማው ደንበኞች ፎረም ተጠሪነቱ ለመ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ይሆናል፡፡
- የደንበኞች ፎረም የበላይ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለቅ/ጽ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ ይሆናል፡፡
- የቅርንጫፍ ጽ/ቤት የነዋሪዎች ንዑስ ፎረም ተጠሪነቱ ለቅርንጫፍ የነዋሪዎች ፎረም ይሆናል፡፡
አንቀፅ 7
የቅርንጫፍና የከተማ ፎረም ተግባራት
7.1 የነዋሪዎች የፎረም አባላት ተግባር
- ፎረሙ በመ/ቤቱ አገልግሎት አሰጣጥ የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በማንሳት እንዲሁም በመልካም አስተዳደር፣ በኪራይ ሠብሳቢነትና ሌሎች የተስተዋሉ ችግሮች ላይ መፍትሄ እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በመድረኩ በመጠቆም የጋራ ምክክር ውይይት ይደረጋል፡፡ በሚቀጥለው ዙር ስብሰባውም የባለፈው ስብሰባ ውሳኔዎችን አፈፃፀም ይገመግማል፡፡
- የፎረሙ አባላት ወክለው ከመጡት ማህበር፣ድርጅት ወይም አደረጃጀት አኳያ መ/ቤቱ በሚሰጠው አገልግሎትና በሚሠራው የልማት ሥራዎች የደንበኛውን ተሳትፎ ለማረጋገጥ የህዝብ ግንዛቤ ማስጨበጫ፣ማንቂያ እና መሰል ሥራዎች በኃላፊነት በመውሰድ ይሰራሉ፡፡
- የመ/ቤቱን የመልካም አስተዳደር ዕቅድ እና ዕቅድ አፈፃፀም በመገምገም ከማስተካከያ ጋር ያፀድቃሉ፡፡
- የፎረሙ አባላት በማንኛውም ወቅት የመ/ቤቱን አገልግሎት በተመለከተ የሚሰጡ ጥቆማዎች እና አስተያየቶች በመሰብሰብ ከፎረሙ በፊት ለሚመለከተው ቅርንጫፍ ኃላፊና ሙያተኞች ማሳወቅና ያልተስተካከለ ከሆነም በፎረሙ ላይ ማቅረብ እና ወይይት እንዲደረግበት ማድረግ፤ በሌላ ጎኑ የተለያዩ ኃይሎች መ/ቤቱን በተመለከተ የሚሰነዝሯቸውን የተሳሳቱ ኃሳቦች ለማረም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ይሠራሉ፡፡
- የፎረሙ አባላት በየአካባቢና የሥራ ቦታቸው በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ያስተዋሉትን ችግር በማናቸውም ግዜ አፋጣኝ የመፍትሄ እርምጃ እንዲወሰድ ጥቆማ ለቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ፣ ለሌሎች የሚመለከታቸው የመ/ቤቱ ሰዎች ወይም ለኮሚኒኬሽን ጉዳዬች ደ/የሥ/ሂደት በሰዓቱ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፡፡
- የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት በስታንዳርዱ መሰረት መተግበራቸውን ይከታተላል፣ ይገመግማል፡፡
- የፎረሙ አባላት እንደተወከሉበት ተቋም፣ ማሕበር፣ አደረጃጀት ወዘተ. የመገኛ አካባቢ (አመቺነት) የባለሥልጣን መ/ቤቱ አገልግሎት ሰጪ ቅ/ጽ/ቤት አመራሮችና ፈፃሚዎች (ቴክኒሺያኖች፣ መሐንዲሶች፣ ሾፌሮች፣ ክለርኮች ወዘተ.) አድራሻ፣ ስምና የሥራ ኃላፊነታቸውን መረጃ በመያዝ በሥራ አካባቢያቸው ለሚታዩ የሥራ ግድፈቶች እና ብልሹ አሠራሮች ፎረሙ የሚካሔድበትን ጊዜ ሳይጠብቁ ጥቆማ በየጊዜው ይሰጣሉ፡፡
- በቅ/ጽ/ቤት ደረጃ በሚደረጉ የፎረሙ ውይይቶች አባላቱ በስልክ ወይም በአካል ለባለሥልጣን መ/ቤቱ ባለሙያዎች በንዑስ አንቀፅ 7.1 በተራ ቁጥር 7 መሠረት የተጠቆሙ ችግሮችና አስተያየቶች ላይ የተሠሩ የማስተካከያ ሥራዎች ያሉበትን ደረጃና ውጤት መገምገም አንዱ ተግባር ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ችግር ያለባቸውን ፈፃሚዎችም ሆነ አመራሮች አንድ በአንድ በስም በማንሳት ይገመግሟቸዋል፡፡
- ከፎረሙ አባላት በሚሰጡ ጥቆማዎች መሠረት በተደጋጋሚ ለሦስትና ከዚያ በላይ ጊዜ ችግር የታየባቸው አመራሮችና ፈፃሚዎች ከሥራ ኃላፊነት ቦታቸው ሕግና ደንቡን በጠበቀ መልኩ ይነሳሉ፡፡ ይህ ውሳኔ ተፈፃሚ የሚደረገው የፎረሙ አባላት የሚያቀርቡት ተጨባጭና አሳማኝ ጥቆማ እንዲሁም በፎረሙ ውይይት ላይ መግባባት በተደረሰበት መልኩ ነው፡፡ ነገር ግን ጥፋቱ የተሠራው ሆን ተብሎ አለያም የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር የሚስተዋልበት ከሆነ በማንኛውም ሰዓት ጥቆማው እንደቀረበ የባለሥልጣን መ/ቤቱ ሕግና መመሪያ በጠበቀ መልኩ እርምጃ ይወሰዳል፡፡
- የንዑስ ፎረሙ ተግባር እና ኃላፊነት
- የከተማ ፎረም አባላት በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ሥር ከተዘረሩት ተግባራት በተጨማሪ በከተማ ፎረም ላይ ከቅርንጫፍ ፎረም ጋር ተያይዞ የተደረጉ እንቅስቃሴዎችና ውጤት፣ የተሰሩ ሥራዎችን በመጥቀስና በቀጣይ መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮችን በመጠቆም ይወያያሉ፣ ይገመግማሉ፡፡
- በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 7.1 ሥር የተዘረዘሩትን ተግባራት ይፈፅማሉ፡፡
- በየወሩ እየተገናኙ ይመክራሉ፤ ሥራን ይገመግማሉ በቀጣይ መፍትሔሐ የሚሹ ጉዳዮችን ይጠቁማሉ፡፡
- በቅርንጫፍ የበላይ ኮሚቴ ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ 3 ሰዎችን ከመካከላይው መርጠው ለቅርንጫፍ ያሳውቃሉ፡፡
7.3 የፎረሙ የበላይ ኮሚቴ ተግባር
- የፎረሙ አባላት ሥራቸውን በአግባቡ እየሰሩ መሆኑን ይከታተላል፡፡
- በየሳምንቱ እየተገናኘ በፎረሙ አቅጣጫ የተሰጠባቸውን ጉዳዮች አፈፃፀም ይገመግማል፣ አቅጣጫ ይሰጣል፡፡
- ኃላፊነታቸውን ባግባቡ የማይወጡ የፎረም አባላት ከአባልነት እንዲሰናበቱና በሌላ እንዲተኩ ለሚመለከተው ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ምክንያቱን በመግለፅ ያሳውቃሉ፡፡
- ከተቀመጠው ጊዜ ሳያልፍ ከከተማ ጋር በመነጋገር የፎረም ስብሰባ ይወስናል፡፡
- ለፎረሙ ተብሎ የሚወጣ ወጭ ሁሉ በህግና በመንግስት መመሪያ መሠረት ለተባለለት አላማ መዋሉን ያረጋግጣል፡፡
7.4 የፎረም ሰብሳቢና የቅርንጫፉ ተግባር
- የፎረሙን ውይይት ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር ሆኖ ይመራል፡፡
- በውይይቱ የታወቁ ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፤ችግሮች አፋጣኝ ምልሽ እንዲያገኙ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፡፡ በየጊዜውም የፎረሙ ስብሰባ ከመካሄዱ በፊት ለውጦችን ይገመግማል ተገቢውን ማስተካከያም ያደርጋል፡፡
- የቅርንጫፍ ፎረም የሚካሄድበትን ግዜ/የጊዜ ሠሌዳ/ እያንዳንዱ ቅርንጫፍ ከመ/ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ደ/የሥ/ሂደት ጋር በመነጋገር ያወጣል፡፡ ሆኖም ሁሉም ቅርንጫፎች በ1 ሳምንት ጊዜ ውስጥ ውይይታቸውን ማጠናቀቅ አለባቸው፡፡
- የቅርንጫፍ ፎረም ስብሰባን በፕሮግራም መሠረት የማካሄድ ኃላፊነት የሚመለከተው ቅርንጫፍ ፅ/ቤት እና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የሥራ ሂደት እና የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ነው፡፡
- የሚመለከተው ቅርንጫፍ በፎረሙ ውይይት ወቅት የተገኙ አባላትን መረጃ በማስፈረም /አቴንዳንስ/ ይይዛል፡፡ ከስብሰባው 10 ቀን ቀደም ብሎም በስልክና በደብዳቤ በትክክል የስብሰባውን ቀንና ቦታ ለእያንዳንዱ አባል ያሳውቃል፡፡ የኮመኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የሥራ ሂደትም በሬዲዮ የስብሰባውን ጥሪ ያስተላልፋል፡፡
- የሚመለከተው ቅርንጫፍ በሚያካሂደው የፎረም ውይይት ቃለ ጉባኤ በመያዝ በተገቢው ሁኔታ ያስቀምጣል፡፡ሲጠየቅም ያቀርባል፡፡ ከውይይቱ በኋላ ባሉት 5 ተከታታይ ቀኖች ዝርዝር ሪፖርት ለኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የሥራ ሂደት ይልካል፡፡ ይህም አካል በሬዳዮ ማብራሪያ ይሰጣል፡፡
- የቅርንጫፍ ፎረም አባላትን በአንቀፅ 6(9) የተቀመጠውን ስብጥር በመጠበቅና ከክፍለከተማና ወረዳ ጋር በመቀናጀት አባላቱን ይመርጣል፤ ያደራጃል፡፡ ይህ ሁኔታ እንደ ከተማ የኮሙኒኬሽን ጉዳይ ያስተባብራል፡፡
- ቅርንጫፎች ለከተማ ፎረም ተሳታፊ የሚሆኑ 50 አባላት ከቅርንጫፉ ፎረም ንቁ ተሳትፎንና እንቅስቃሴን መሠረት በማድረግ በመምረጥ ዝርዝሩን ለመአከሉ ለህዝብ ግንኙነት ያሳውቃሉ፡፡ የህዝብ ግንኙነት ክፍልም የተሟላ መረጃ ይይዛል፡፡
- የፎረሙ የበላይ ኮሚቴ በአንቀጽ 6(8) የተቀመጠው ስብጥር በመጠበቅ እንዲሰየም ይደረጋል፡፡
- ቅርንጫፉ ለፎረም አባላቱ አባልነታቸውን የሚገልፅ መታወቂያ ይሠጣል፡፡
- አገልግሎት አሠጣጥና መልካም አስተዳደር የያንዳንዱ ፎረም አጀንዳ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖከ ፎረም ከአባሉ ጥያቄ ወይም በራሱ ቅርንጫፍ አጀንዳ ይቀርፃል፡፡
- ቅርንጫፎች የቅርንጫፍም ሆነ የከተማ ፎረም ከመካሄዱ 10 ቀን ቀድመው ጥሪ ለአባላቱ እንዲደርስ ካደረጉ በኋላ ከ5 ቀን በፊት ሁሉምጥሪውን መስማታቸውን በስልክ ያረጋግጣሉ፡፡
- የሁሉም ዓይነት አደረጃጀቶች (የነዋሪዎች ፎረም፣ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ፣ የፎረም የበላይ ኮሚቴ ስብሰባዎች) ሳይቆራረጡ በተቀመጠላቸው ጊዜ ውስጥ መካሄዳቸው ይከታተላል፣ የውይይት አጀንዳውም ይቀርፃል፡፡
7.5 የቅርንጫፍና የከተማ ፎረም ምክትል ሠብሳቢዎች ተግባር
- የፎረሙን ውይይት ሠብሳቢው በሌለበት ግዜ ሰብሳቢውን ተክተው ይመራሉ፡፡ ፎረሙም ስብሰባው የሚሰጠውን ሥራ ይሰራል፡፡
- በውይይት የታወቁ ጠንካራ ጎኖች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፤ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ይከታተላሉ፤ለሚመለከታቸው ክፍሎች ያሳውቃሉ፡፡
7.6 የቅርንጫፍና የከተማ ፎረም ፀሀፊ ተግባር
- በፎረም ስብሰባ የተገኙ አባላትን መረጃ /አቴንዳንስ/ በማስፈረም ይይዛል፡፡
- የነዋሪዎችን ስብሰባ ጥሪ በአግባቡ ያስተላልፋል፡፡
- በፎረም ስብሰባ ቃለ ጉባኤ በመያዝ በተገቢው ሁኔታ ያስቀምጣል፡፡ሲጠየቅም ያቀርባል፡፡
- የፎረሙን ውይይት ውጤት ጨምቆ በሪፖርት መልኩ ለስብሰባው ያቀርባል፡፡
7.7 ከደንበኞች ፎረም ጋር ተያይዞ የህዝብ ግንኙነት ደ/የሥ/ሂደት ተግባር
- የደንበኞች ፎረም ስብሰባ ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ የሚመለከታቸውን ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ያግዛል፡፡ በሬዲዮም ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
- የፎረም አባላት በምክክር መድረኩም ይሁን በአካል ቀርበው የሚያነሷቸውን ጠንካራ ጎኖችና ችግሮች መረጃ ይይዛል፤ተገቢው ምላሽ እንዲያገኝ ለሚመለከታቸው ክፍሎች ያሳውቃል፤ተገቢውን የህዝብ ግንኙነት ሥራዎቹን ይሠራል፡፡
- ከየቅርንጫፉ የሚላኩለትን የአባላት መረጃ በመያዝ የከተማ ፎረም አባላት እነማን እንደሆኑ የሚያሳይ መረጃ ይይዛል፡፡
- የከተማ ፎረም የሚካሄድበትን ግዜ/የጊዜ ሠሌዳ/ በሚመለከት ከመ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር በመነጋገር ያወጣል፡፡ ለቅርንጫፎችም ያሳውቃል፡፡
- የከተማ ፎረም በወቅቱ እንዲካሄድ ያደርጋል፡፡ የአባላትን መረጃም አደራጅቶ ይይዛል፡፡
- በአገልግሎት አሠጣጥና መልካም አስተዳደር የቅርንጫፍ እንቅስቃሴና ሌሎች መወያያዎችን ጨምሮ ለከተማ ፎረም አጀንዳ ይቀርፃል፡፡
- የውይይት ሪፖርት ከቅርንጫፎች ተቀብሎ በመቀመር የከተማው ፎረም ከመጀመሩ በፊት ለባለሥልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ያቀርባል፡፡ ከውይይት በኋላም የህዝብ ግንኙነት ሥራዎችን በሚዲያ ጭምር ያሰራል፡፡
አንቀጽ 8
የፎረሙን አባላት መተካት
- በአንቀጽ 7 (7.1.) የተመለከቱትን ተግባራት በአግባቡ የማያከናውኑ የፎረሙ ማህበራት ኃላፊነታቸውን እንዳልተወጡ ይቆጠራል፣
- ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ የፎረሙ አባላትን የፎረም የበላይ ኮሚቴው ተከታትሎ ከጠቅላላ ጉባኤ አባላት ጋር በመወያየት ከአባልነት እንዲሰናበቱ ለሚመለከተው ቅ/ጽ/ቤት ምክንያቱን በመግለጽ የሚያሳውቅ ይሆናል፣
- የሚመለከተው ቅ/ጽ/ቤትም ከበላይ የፎረም ኮሚቴ የቀረበለትን ጥያቄ በመቀበል በአንቀጽ 6 (9) የተቀመጠውን የፎረሙ አባላት ስብጥር ጠብቆ አባሉ በሌላ እንዲተካ ያደርጋል፣
አንቀጽ 9
የቅርንጫፍ ጽ/ቤት እና የከተማ ፎረም አካላት የተጠያቂነት አግባብ
በቅ/ጽ/ቤት የሚካሄደው የደንበኞች ፎረም የቅ/ጽ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ እና የክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ በጋራ በመሆን የሚመሩት ይሆናል፡፡ በተጨማሪም በከተማ ደረጃ በሚካሄደው የደንበኞች ፎረም የከተማ ስራ አስኪያጅ ቢሮ ዋና ኃላፊ እና የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ በጋራ ይሰበስባሉ፡፡ በመሆኑም በየደረጃው ለሚኖረው የፎረሞች ተፈጻሚነትን ለማረጋገጥ የሚከተሉት ተጠያቂነት አለባቸው፡፡
- በቅ/ጽ/ቤቶች ደረጃ በሚካሄዱ ፎረሞች የመቆራረጥ፣ የፎረሙን ዋና አላማን እና ይዘቱን ማስጠበቅ አለመቻል፣ የፎረሙን አባላት በሚካሄዱ ውይይቶች በአግባቡ አለማስተናገድ የመሳሰሉት ክፍተቶች ሲፈጠሩ “የፎረሙ የበላይ አካላት” በጋራ ተጠያቂ ናቸው፣
- በተመሳሳይ በከተማ ደረጃ በሚካሄዱ ፎረሞች የመቆራረጥ፣ የፎረሙን ዋና አላማን እና ይዘቱን ማስጠበቅ አለመቻል፣ የፎረሙን አባላት በሚካሄዱ ውይይቶች በአግባቡ አለማስተናገድ የመሳሰሉት ክፍተቶች ሲፈጠሩ “የፎረሙ የበላይ አካላት” በጋራ ተጠያቂ ናቸው፣
- የክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ በህዝብ የተወከለ እና ህዝባዊ ጥያቄዎችን መፍታት እና አግባብነት ያለው ወቅታዊ የህዝብ ጥያቄዎችን መመለስ ዋነኛ ኃላፊነቱ እንደመሆኑ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ፎረም በኃላፊነት ሳይመራ በማንኛውም ወቅት ከባለስልጣን መ/ቤቱ ጋር በተያያዘ
- ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ወደ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መግፋት እና ከኃላፊነት መሸሽ አይችልም፣ ለዚህም በከተማ አስተዳደር ቻርተር መሰረት የተደነገጉ አንቀጻች (የህዝብን ጥያቄ መቀበል እና መፍታት አለመቻል) ባለማስፈፀም ተጠያቂ ይሆናል፣
- የቅ/ጽ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ እና ማኔጅመንት ወይም የቅርንጫፍ የበላይ አመራሮች ፎረሙን በአግባቡ ባለመምራቱ በባለስልጣን መ/ቤቱ የስራ አመራር መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ኃላፊነትን ባለመወጣት ተጠያቂ ይሆናል፣
- በከተማ ደረጃ ለሚካሄደው ፎረም የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋ/ስራ አስኪያጅን ጨምሮ ማኔጅመንቱ፣ የኮሙኒኬሽን ደጋፊ የሥራ ሂደትና ጉዳዩ የሚመለከተው ኃላፊ ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ መንግስትና ህዝብ የተሰጠውን ኃላፊነት ባለመወጣት ከኃላፊነት መነሳትን ጨምሮ በመ/ቤቱ የሥራ አመራር መተዳደሪያ ደንቦች እና በሥራ አመራር ቦርድ ውሳኔ መሰረት ተጠያቂ ይሆናል፣
አንቀፅ 10
የፎረሙ ስብሰባ ጊዜ
- የእያንዳንዱ ቅርንጫፍ የነዋሪዎች ፎረም ስብሰባ በሦስት ወር አንድ ግዜ በዓመት አራት ጊዜ መካሄድ ይኖርበታል፡፡እንደአስፈላጊነቱ ስብሰባው ከዚህ ባጠረ ጊዜ ሊጠራ ይችላል፡፡ የተለየና አስገዳጅ ነገር ካላጋጠመ በስተቀር ከተቀመጠው ጊዜ ስብሰባው አያጥርም፡፡
- የከተማ ፎረም ስብሰባ በዓመት ሁለት ግዜ ይካሄዳል፡፡ ጊዜው ከዚህ ሊያጥር ቢችልም አስገዳጅ ሁኔታ ካላጋጠመ በስተቀት ከ6 ወር መዝለል የለበትም፡፡
- “የፎረም ጠቅላላ ጉባኤ” በየወሩ መደበኛ ስብሰባውን ያካሂዳል፡፡ የስብሰባ ጊዜው ከዚህ አያልፍም፡፡
- የፎረሙ የበላይ ኮሚቴ በየ15 ቀኑ እየተገናኙ ስራን ይገመግማሉ፡፡ ይህን ጊዜ ማሳለፍ አይችልም፡፡
ክፍል ሦስት
ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
አንቀፅ 11
ስለ አበል
- የከተማም ሆነ የቅርንጫፍ የፎረም እያንዳንዱ አባል በስብሰባው በተሳተፈ ጊዜ የትራንስፖርትና የምሳ አበል እንዲሁም ከስብሰባ ውጭ በተደጋጋሚ ጊዜ ገንቢና እውነተኛ ጥቆማ፣አስተያየትና መረጃ ለሚሰጡ የፎረም አባላት በቀጣይ ባለስልጣኑ በሚያወጣው ተጨማሪ አሰራር መሰረት በሚቀመጠው መስፈርት አግባብ አበል ይከፈላል፡፡
- ዘወትር በሥራ ላይ ለሚገኙ “የፎረሙ የበላይ ኮሚቴ” አባላት ለሥራ አፈፃፀማቸው እንዲረዳቸው የሥልክ አበል በየወሩ ብር 50/ሃምሳ ብር/ ይከፈላቸዋል፡፡ በመ/ቤቱ የሰርቪስ መኪኖች በየትኛውም ጊዜ በሚሰጣቸው መታወቂያ መሠረት ትራንስፖርት እንዲጠቀሙ ይፈቀድላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ከመካከላቸው በግል ለሚያበረከረቱት ገንቢና እውነተኛ ጥቆማ በማድረግ፣ አስተያየት በመስጠት፣ ችግር ያለባቸውን የመ/ቤቱ አባላትና ሌሎችንም በማጋለጥ ለሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በቀጣይ ባለስልጣኑ በሚያወጣው የማበረታቻ አሰራር መሰረት ማበረታቻና እውቅና ይሰጣቸዋል፡፡
- ከምሣ፣ ከሻይና ቡና አበል ውጭ የስልክና የሌሎች ማበረታቻና ጥቅማጥቅም እንዲሁም የትራንስፖርት ጉዳይ ክፍያዎች በተለየ ሁኔታ በባለሥልጣኑ ሥራ አስኪያጅ ካልተፈቀደ በቀር ለመ/ቤቱ ሠራተኞች አይሰጥም፡፡