የውሃ ፍሳሽ ታሪክ

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን

አመሰራረት አጭር ታሪክ

1. አመሠራረት

የአዲስ አበባ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 68/1963 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ፤ በድጋሚ በአዋጅ ቁጥር 10/87 በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን መቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ተቋቋመ፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱ በአዋጅቁጥር 10/87 በተሰጠው ስልጣን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የውሀና ፍሳሽ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የውሀ መገኛዎችን በመጠቀም እና የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓትን በመዘርጋት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ከአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን ዕድገት ጋር የሚመጣጠን የንፁህ ውሀ አቅርቦት እና የዘመናዊ ፍሳሽ ማስወገጃ አገልግሎት ለከተማዋ ነዋሪ በበቂና በአስተማማኝ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ ስምንት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን በማዋቀር በእነዚህ ቅ/ጽ/ቤቶች አማካኝነት ለህብረተሰቡ አስፈላጊውን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪ የቧንቧ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆነው በ1893 ዓ.ም. ነበር፡፡ ይህም የአፄ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት የውሃ አገልግት ተጠቃሚ በሆነ ሰባት ዓመታት ቆይቶ ነው፡፡ የቧንቧ ውሃ አገልገሎት መጀመርን ተከትሎ አገልግሎቱን ማን ይስጠው የሚለውን መልስ መሻትም ግድ ነበር፡፡ በመጀመሪያ የሥራ ሚኒስቴር በመባል ይታወቅ የነበረው መ/ቤት ይህን ኃላፊነት ሲወጣ ቆየ፡፡ ከጣሊያን ወረራ በኋላ በ1934 ዓ.ም. የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት እንደገና ሲዋቀር ደግሞ “የውሃ ማደረጃ ዋና መ/ቤት” በሚል ስያሜ እንደ አንድ የሥራ ክፍል የውሃ አገልግሎት የሚሰጥ ክፍል ተቋቋመ፡፡

የውሃ አገልግሎት አጀማመር

ባለሥልጣን መ/ቤቱ በአሁኑ ወቅት ከ480ሺ በላይ የውሃ ደንበኞች ያሉት ሲሆን ከገፀ ምድርና ከከርሠ ምድር የውሃ መገኛዎቹ በየዕለቱ 608ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ እያመረተ ያሠራጫል፡፡ ዋና ዋና የውሃ መገኛዎቹም የሚከተሉት ናቸው፡-

· የገፈርሣ ግድብና ማጣሪያ ጣቢያ (በቀን 30ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ የማምረት አቅም አለው)

· የለገዳዲ ግድብና ማጣሪያ ጣቢያ (የድሬ ግድብን ጨምሮ በቀን 195ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ የማምረት አቅም አለው)

· ጉድጓዶችና ሌሎች የከርሠ ምድር ምንጮች (በቀን 383ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ የማምረት አቅም አላቸው)

ከነዚህ መካከል በ1930ዎቹ መጀመሪያ የተወጠነው የገፈርሣ ግድብ ከሁሉም አንጋፋው ነው፡፡ ግድቡ ለ70 ዓመታት ካገለገለ በኋላ በ2000 የበጀት ዓመት የማጠናከሪያ ፕሮጀክት ተካሒዶለታል፡፡

ይህም በአገልግሎት ብዛት አጥቶት የነበረውን አቅም መመለስ ያስቻለ ነበር፡፡

የለገዳዲ ግድብና ማጣሪያ ጣቢያ በ1963 ዓ.ም. ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት አቅሙን ማሳደግ ያስቻሉ የማስፋፊያ ሥራዎች የተከናወኑለት ሲሆን በቅርቡ የተካሔደለት የማስፋፊያ ሥራ በቀን 30ሺ ሜትር ኪዩብ ተጨማሪ ውሃ ማምረት የሚያስችል አቅም ፈጥሮለታል፡፡

በ1980ዎቹ መጨረሻ በከተማዋ የውሃ አቅርቦትና ፍላጎት መካከል የተፈጠረውን ሰፊ ክፍተት በአጣዳፊ መርሐ ግብር ለመሙላት የከተማዋ አስተዳደር መወሰኑን ተከትሎም የድሬ ግድብና የመጀአቃቂ ከርሠ ምድር ውሃ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት ላይ ውለዋል፡፡

ከዚህ በኋላም በአቃቂ እና በለገዳዲ የከርሠምድር ውሃ መገኛዎች እንዲሁም በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ቁጥራቸው ከ100 የሚልቅ ጥልቅ እና መካከለኛ ጉድጓዶች ተቆፍረው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲያውም በአሁኑ ወቅት ከተማዋ አብዛኛውን ውሃዋን እያገኘች ያለቸው ከከርሠ ምድር የውሃ መገኛዎች ነው፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የውሃ አቅርቦትና የፍሳሽ ማስወገድ አገልግሎት ፍላጎት በተሻለ አኳኋን ለማቅረብ እንዲቻል የዘርፉን አገልግሎቶች ዋነኛ ትኩረቱ አድርጎ የሚንቀሳቀስ መ/ቤት ማቋቋም አስፈለገ፡፡ በዚሁ መሠረትም በአዋጅ ቁጥር 68/1963 “የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለሥልጣን” በሚል ሥያሜ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ተቋቋመ፡፡ በ1987 ዓ.ም. ደግሞ ለባለሥልጣኑ ተጨማሪ ሥልጣን በመስጠት “የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን” በሚል መጠሪያ መ/ቤቱ እንደገና ተቋቁሟል፡፡

የፍሳሽ ማስወገድ አገልግሎት አጀማመር

የፍሳሽ ቆሻሻ የማስወገድ አገልግሎት በከተማችን አዲስ አበባ የተጀመረው በ1928 ገደማ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከተማዋ በተቆረቆረችባቸው መጀመሪያ ዓመታት ፍሳሽ ቆሻሻ እምብዛም ችግር የሚፈጥር ጉዳይ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም አዲስ በተቆረቆረችው አዲስ አበባ የከተማ ቦታ በስፋት ይገኝ ስለነበር ኗሪዎች መፀዳጃ ቤት ሲሞላባቸው እየደፈኑ ሌላ መቆፈር የሚችሉበት ሁኔታ በመኖሩ ነበር፡፡

ነገር ግን ቀን አልፎ ቀን ሲተካ፣ የኗሪው ቁጥርም እየጨመረ ሲመጣ የቦታ ነገር እንደልብ የሚገኝ አልሆነም፡፡ይህ ሁኔታ ደግሞ መፀዳጃ ቤቶችን ለዘለቄታው መጠቀምን ውዴታ የግዴታ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽን ለማስወገድ ትኩረት መስጠት ግድ መሆኑን መገንዘብ በ1920ዎቹ መጨረሻ ገደማ ፍሳሽን በመስመር የማስወገድ አገልግሎት እንደተጀመረ ይነገራል፡፡

በተሽከርካሪ ፍሳሽ የማስወገድ አገልግሎትም ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ነው፡፡ በ1963 ዓ.ም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን መ/ቤት ራሱን ችሎ እንዲቋቋም ሲደረግ አገልግሎቱን ሲሰጥ ነበረው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ያገኛቸውን ከአምስት ያልበለጡ የፍሳሽ ተሽከርካሪዎች በመያዝ ነበር ከውሃው ጎን ለጎን የፍሳሽ ሥራውንም በኃላፊነት ማከናወን የጀመረው፡፡ ከዚህም የፍሳሽ ዘርፉ አገልግሎት ረዥም ዘመን ያስቆጠረ መሆኑን ነው፡፡

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ከተቋቋመበት ዋና ዋና ዓላማዎች አንዱ በከተማው ውስጥ የሚፈጠረውን የፍሳሽ ቆሻሻ ማሰባሰብ፣ ማጣራትና ማስወገድ ነው፡፡ ነገር ግን ባለፉት ዓመታት ከተማዋ ካለባት የሀብት ውስንነት አኳያ ትኩረቷን በውሃው ዘርፍ ላይ አድርጋ በመቆየት የፍሳሽ አገልግሎቱ በሚፈለገው ደረጃ አላደገም፡፡ ከተማዋ ሁሉን አቀፍ ፈጣን እድገት ተከትሎ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መጣው የዘመናዊ ሕንጻ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታዎች ጋር ተያይዞ የመጣውን የፍሳሽ ማንሳት አገልግሎት ፍላጎት ለሕዝቡ ምላሽ ለመስጠትና ንጹህ የመኖሪያ አካባቢን ለመፍጠር የፍሳሽ ማስወገድ መሠረተ ልማት ግንባታ እንደ አዲስ ለመጀመር በ2003 ዘርፉ ትኩረት እንዲያገኝ በማድረግ በአዲስ መልክ አደረጃጀቱ እንዲስተካከል ተደርጓል፡፡