የስራ አስኪያጅ መልእክት

ከ 5 ሚሊየን በላይ ህዝብ የሚኖርባት ከተማችን አዲስ አበባን ለኑሮ፣ ለስራና ለጉብኝት ምቹ ለማድረግና አስፈላጊውን መሠረተ ልማት በምታሟላበት ቁመና ላይ ለማድረስ መንግስት ሠፊ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ የከተማዋን የመሰረተ ልማት አቅርቦት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ከመጣው ፍላጎት ጋር ለማጣጣም ከሌሎች የልማት ስራዎች በተጓዳኝ የውሃ አቅርቦት ሽፋኑን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግስታችን ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ለውሃ ፕጀክቶች ስራ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በተመሳሳይ መልኩም የፍሳሽ ማንሳት አገልግሎቱን ለማሳለጥ ያስቻሉ የፍሳሽ ማንሻ ተሽከርካሪዎች ግዢና  የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ግንባታና የፍሳሽ መረብ ማስፋፊያ ሥራዎች ተወጥነው ከግብ ደርሰዋል፡፡ በተለያየ የግንባታ  ሒደት ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችም አሉ፡፡

በተለይም በውሃ አቅርቦት ሥራ ረገድ የአዲስ አበባ ከተማን የውሃ ፍላጎት ከገፀ-ምድና ከከርሰ ምድር የውሃ ምንጮች ለማሟላት ባለሥልጣን መ/ቤቱ ከሚመለከታቸው የመንግስትና አበዳሪ አካላት ጋር በመቀናጀት የአጭር እና የረጅም ጊዜ የሚተገበሩ ዕቅዶች አዘጋጅቷል፡፡ ከነዚህም መካከል ከፊሎቹን ባለፉት አመታት ተግባራዊ በማድረግ አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ የውሃ አቅርቦቱ ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ መልኩ የከተማዋን ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር የወደፊቱን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ለማስቻልም በጥናት የተደገፉ ግንባታዎች በማከናወን ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህ ሂደትም እስከ 2007 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ 350ሺ ሜትር ኪዩብ የነበረውን የከተማዋን የውሃ አቅርቦት ሽፋን 464 ሺ ሜትር ኩብ በቀን ማድረስ ያስቻሉ ፕሮጀክቶች ተጠናቀዋል፡፡ በ2008 የበጀት ዓመትም የለገዳዲ ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮ ፕሮጀክትን፣ የአቃቂ ከርሰምድር ምዕራፍ 3ሀ እና በዚሁ በአቃቂ አከባቢ ምርት መስጠት ባቆሙ ጉድጓዶች ምትክ የተቆፈሩ 5 ጉድጓዶችን አጠቃላይ ሥራ በማጠናቀቅ በድምሩ 128 ሺ ሜትር ኩብ ውሃ ወደ ሥርጭት ማስገባት ችለናል፡፡ ይህም የከተማዋን ዕለታዊ የውሃ አቅርቦት ወደ 592ሺ ሜትር ኪዩብ አሳድጎታል፡፡ ይህም 670 ሺ ከሆነው የወቅቱ የከተማዋ የውሃ ፍላጎት አንፃር ሲታይ ሽፋኑን  90% ገደማ ያደርሰዋል፡፡

ምንም እንኳን በዚህ የበጀት ዓመት ያከናወንናቸው እነዚህ ሥራዎች በከተማዋ የውሃ አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ልዩነት ሙሉ በሙሉ መድፈን ባይስችሉም ከ1ሚሊዮን በላይ የከተማዋ ኗሪዎችን የተሻለ የውሃ አቅርቦት ተጠቃሚ ማድረጋቸው እሙን ነው፡፡ በቀጣይም የከተማዋን የውሃ ፍላጎት ለዘለቄታው ለማሟላት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን በሙሉ ትኩረት ለማከናወን የሚኖራቸው ሚናም በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡

በተመሳሳይ የፍሳሽ አገልግሎቱን ለማስፋፋትም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በትኩረት ስንሠራ ቆይተናል፡፡ በተለይ ፍሳሽን በተሽከርካሪ በማንሳት አገልግሎት ረገድ ያሉ ማነቆዎችን ለማስወገድ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የ45 ተሸከርካሪዎች ግዢ በመፈፀሙና በተጓዳኝ ሥራ ላይ ባዋልናቸው የመልካም አስተዳደር ዕቅዶች ምክንያት ከዚህ ቀደም ደንበኛው አገልግሎቱን ለማግኘት ጥያቄ ባቀረበ በአማካይ እስከ ሦስት ወር ይቆይ የነበረውን የወረፋ ጊዜ እጅግ ቢዘገይ እስከ ሳምንት ወደ ሚደርስ ጊዜ ማሳጠር ተችሏል፡፡

ያም ሆኖ የዘርፉ ችግር በማያዳግም ሁኔታ ሊፈታ የሚችለው የተሸከርካሪ ቁጥርን በመጨመር ሳይሆን የፍሳሽ መረቡን ተደራሽነት በማሳደግ በመሆኑ ለዚሁ ተግባር ልዩ ትኩረት ሰጥተናል፡፡ በዚህም መሠረት የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያን ፍሳሽ የማጣራት አቅም አሁን ከሚገኝበት 7,500 ሜትር ኪዩብ ወደ 100,000 ሜትር ኪዩብ ለማሳደግ የሚያስችል ፕሮጅከት ከ100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ በመካሔድ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ፕሮጀክት የፍሳሽ መረቡን በማስፋፋት 1.2 ሚሊዮን ያህል የከተማዋን ኗሪ  የዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገድ አገልግሎት ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

በአጠቃላይ ባለሥልጣን መ/ቤቱ የከተማዋን ኗሪ የውሃ አቅርቦትና የፍሳሽ ማስወገድ አገልግሎቶች ፍላጎት ለማሟላት በቀጣይ የሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን ዓመታት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ሰፊ ዝግጅት አድርጓል፡፡ በነዚህ ዓመታት የዘርፉ አገልግሎቶች የላቀ ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ እንጠብቃለን፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንደ ግብዐት በመውሰድ የአገልግሎት አሰጣጥ ግድፈቶችን ማስወገድና የተሻለ የአገልግሎት አሰጣጥ ማስፈን የሚያስችሉ ጅምር ሥራዎችም አሉን፡፡ እነዚህን አጠናክረንና አዳብረን በመተግበር በብዛትም ሆነ በጥራት የተሻለ አገልግሎት ለማቅረብ በልዩ ትኩረት እንደምንሠራ ለማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡

አመሰግናለሁ!