የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎች ከተገነቡበት ዓላማ ውጪ ወደ ፍሳሽ መስመሮች በሚገቡ ጠጣር ነገሮች፣ ቅባትነት ይዘት ያላቸው ነገሮች፣ ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁ ዝቃጮች እና ወደ ማጣሪያ ጣቢያ የሚገባ ከፍተኛ የሆነ ጎርፍ የቀላቀለ ፍሳሽ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገለፀ፡፡

ባለፈው ዓመት ወደ ስራ የገባውና በቀን 100 ሺህ ሜ.ኪብ ፍሳሽ የማጣራት አቅም ያለው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ በ2011ዓ.ም በዘነበው የበልግ ዝናብ ምክንያት በተለያዩ ክፍሎች ላይ እንዲሁም በባይሎጅካል የማጣሪያ ክፍል ላይ ጉደት በማድረስ ፍሳሽ የማጣራት ሂደቱን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ እና የፍሳሽ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ተስፋለም ባዩ ገልጸዋል፡፡

አቶ ተስፋለም አያይዘውም ባዕድ ነገሮች ማለትም እነደ ቤንዚን፣ ናፍጣ፣ የሞተር ዘይት፣ ኬሚካል፣ ስብና ቅባቶች የቤት ውስጥ ፍሳሽ ቆሻሻን ብቻ ለማጣራት በተገነባው ማጣሪያ ጣቢያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረስ መሆኑን ሀላፊው ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ በ8 ኮዶሚኒየም ሳይቶች በተገነቡ 12 Membren Bio Reactor (MBR) በሚባሉ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያዎች የሚላኩ ላስቲኮች፣ ጨርቃጨርቆች፣ አጥንቶች፣ አሸዋ፣ አፈር ዳይፐርና የፌስታል ቁርጥራጮች በፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮች ለይ እክል እየፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡም በፍሳሽ መሰረተ ልማቶች ላይ ከአጠቃቀም ችግር የተነሳ እየተከሰተ ያለውን ችግር በመረዳት በቀጣይ ክረምት  የዝናብ ጎርፍ ወደ ፍሳሽ መስመር እንዳይገባ የማንሆሎ ክዳኖች እንዳይሰረቁ እንዲሁም ከከፍተኛ ፍሳሽ ቆሻሻ አመንጪ ተቋማት፣ ከጋራዥና ከሆቴል ቤቶች የሚወጡ ዘይት እና ግሪስ የመሳሰሉት ፍሳሾች የሚለቁ  አካላትን ጥቆማ በመስጠት እንዲሁም የፍሳሽ መሰረተ ልማት ደህንነትን ለማስጠበቅ በሚሰሩ ስራዎች ከባለስልጣኑ ጋር ትብብር እንዲያደርጉ አቶ ተስፋለም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ባለስልጣኑ በአሁኑ ወቅት የከተማዋን ፍሳሽ አውጋገድ ዘመናዊ ለማድረግ የፍሳሽ ማስተር ፕላን አዘጋጅቶ በሦስት ተፋሰሶች  ማለትም በቃሊቲ ተፋሰስ፣ በምሥራቅ እና በደቡብ ተፋሰሶች  ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎችን እና የሥርጭት መረብን ያካተተ ሰፊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እያከናወነ ይገኛል፡፡