ባለሥልጣኑ በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚገኙና ለከተማዋ የውሃ መገኛ ለሆኑ የኦሮምያ ልዩ ዞን አከባቢዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ የሰራቸውን ስራዎች ለጋዜጠኞች ያስጐበኘ ሲሆን በወቅቱ እንደተገለፀው ባለስልጣኑ በኦሮምያ ልዩ ዞኖች በሚገኙ አራት ወረዳዎች ማለትም መሪኖ፣ ኤቹ፣ አቃቂና በሰበታ ዙሪያ በጥቅሉ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ 31 የውሃ ቦኖዎችን በመገንባት ከ15 ሺ 500 በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመትም የከተማ አስተዳደሩ 666 ሚሊየን ብር በጀት መድቦ የውሃ መገኛ የሆኑ የአዲስ አበባ ዙሪያ አከባቢዎችን የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በጉብኝቱ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ የመሬኖ አከባቢ ነዋሪዎች መካከል ወ/ሮ ሽቶ ወገን በአካባቢያቸው ከተቆፈረ ጉድጓድ የአዲስ አበባ ነዋሪ ንፁህ ውሃ እየጠጣ  አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ካለመሆኑም በላይ ሴቶች፣ ልጆች እና አቅመ ደካሞች በጣም እየተቸገሩ ስለነበር ነዋሪው ቅሬታውን ሲያሰማ መቆየቱን ገልፀው የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣንም ችግራቸውን አይቶ እና ከአስተዳደራቸው ጋር ተነጋግሮ መፍትሔ ስለሰጣቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ውሃ የሚያገኙበት ሠዓት አነስተኛ በመሆኑ ቢሻሻልልን እና ውሃ በመስመር በየቤቱ ቢገባ  ችግራችንን አስተማማኝ በሆነ መልኩ መቅረፍ ይቻል ነበር የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ወ/ሮ አስራተ በየነ በበኩላቸው የቦኖ ውሃ ተጠቃሚ ከመሆናቸው በፊት በሌሊት ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠውና ረጅም ርቀት ተጉዘው ውሃ ይቀዱ እንደነበር ተናግረው ተማሪዎችም ውሃ የሚያገኙት በፕላስቲክ ጠርሙስ ከየመንደሩ እየለመኑ ነበር፡፡ አሁን ግን ችግራችንን በተደጋጋሚ ለአስተዳደሩ በማቅረባችን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መፍትሔ አግኝተናል ብለዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ወጣት ግርማ ገበየሁ እንደገለፀው የአከባቢው ነዋሪ የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ ባለመሆኑ ቅሬታ አሰምቶ ነበር፡፡ ችግሩም እስኪቀረፍ በትዕግስት ሲጠብቅ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን የወረዳው እና የቀበሌው አስተዳደር ከውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ጋር ባደረገው ውይይት የቦኖ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በፊት ነዋሪው ከጉድጓድ እና ከወንዝ የሚቀዳው ውሃ ንፁህ ስላልነበር ለጉዳት ተጋልጦ ነበር፡፡ አሁን ግን ችግሩ በተወሰነ ደረጃ ቢቃለልም መስኖ የምንጠቀመውና እንስሳት የሚጠጡት ውሃ ከአዲስ አበባ ተበክሎ ከሚመጣው ወንዝ በመሆኑ በተዘዋዋሪ የጤና ችግር እያጋጠመው ነው ብለዋል፡፡

በገላን ወረዳ አስተዳደር የመሪኖ ቀበሌ ም/አስተዳደሪ የሆኑት አቶ በቀለ ሀይሉ በቀበሌያቸው በስፋት ከሚነሱት የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች መካከል የውሃ ችግር ዋነኛውና ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ ችግሩን ለማቃለል የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በቀበሌያቸው ከ4 ሺ በላይ አባወራ እና ከ19 ሺ በላይ እንስሳት መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ በቀለ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የሚሠጠውን ውሃ መጠን ተጨምሮ ህብረተሰቡ የ24 ሠዓት ተጠቃሚ እንዲሆን፣ ለአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ እንዲሁም ለእንስሳት ገንዳ እንዲሠራ ባለሥልጣኑ የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ ሲጠቀም የነበረው ከአዲስ አበባ ተበክሎ ከሚመጣው ወንዝ ስለነበረ ለሞትና ለተለያዩ ችግሮች ሲጋለጥ ቆይቷል ያሉት የወረጢኖ ቀበሌ ገ/ማህበር ሊቀመንበር አቶ አለማየሁ መኮንን በአሁኑ ወቅት ግን በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ድጋፍ ህብረተሰቡ ንፁህ ውሃ እየጠጣ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ለህዝቡም ሆነ ለእንስሳት በቂ የውሃ አቅርቦት እንዲኖርና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከኦሮምያ ክልል አስተዳደር እና ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን እያደረገው ስላለው ድጋፍ እና ህብረተሰቡ እያነሳው ስላለው ጥያቄ በተመለከተ የተጠየቁት የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የስራ ሂደት መሪ አቶ እስጢፋኖስ ብስራት ምላሽ ሲሰጡ  ከዚህ በፊት በአከባቢው ካሉ አመራሮች ጋር ያለውን የውሃ ችግር የቦኖ ውሃ በማቅረብ ለመፍታት ስምምነት ላይ በተደረሰ መሰረት ከመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ እስጢፋኖስ ገለፃ ከህብረተሰቡ “የእንስሳት መጠጫ ገንዳ ይሰራልን” “ውሃ የሚቀርብበት ሠዓት ይራዘምልን” እና “ውሃ በመስመር ወደየቤቱ ይግባልን” የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሳ በመሆኑ ከኦሮምያ ክልል ጋር በመቀናጀት እና ከሌሎች አጋዥ ድርጅቶች ጋር በመሆን አቅም በፈቀደ ችግሮችን ለመፍታ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡