የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሚያቀርበውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሳደግ እና የፍሳሽ ማንሳት፣ ማጣራትና ማስወገድ አገልግሎት ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ በየዓመቱ የተለያዩ ተግባራትን እየፈጸመ ይገኛል፡፡

ይሁንና ስራዎችን በአግባቡና የህብረተሰቡን ጥያቄና ፍላጎት በሚመለስ ሁኔታ ለማከናወን ደግሞ የሁሉም ፈጻሚዎች እኩል አስተዋጽኦ አስፈላጊ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ስለሆነም የልማታዊ ሰራዊት ግንባታ ላይ ሰፊ ስራ በመስራት የአመራሩንና የፈጻሚውን የእውቀት፣ የአመለካከትና የክህሎት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ስልጠና በየጊዜው ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ይህንም ተግባራዊ ለማድረግ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል የስልጠና ሰነድ ተዘጋጅቶ በ17 መድረኮች በሁለት ዙር በመክፈል ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ስልጠናው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን፣ የዜጎች ቻርተርን፣ የቢ.ፒ.አር እና ቢ.ኤስ.ሲ ቅንጅታዊ ትግበራን፣ የልማት ሰራዊት ግንባታን፣ የተቋሙ የአሰራር መመሪያዎችን፣ የቴክኖሎጂ ትግበራን፣ እንዲሁም የካይዘን አተገባበር እና የስብሰባ መመሪያዎችን በሰፊው ዳሷል፡፡

በዚህ ስልጠና በሁለቱም ዙሮች የሰለጠኑ የተቋሙ ሰራተኞች ስልጠናው አቅም ገንቢ መሆኑን እና ጥሩ ግንዛቤ እንዳስጨበጣቸው አስታውሰው ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ስልጠናዎች ቀጣይነት ሊኖራቸው አንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በማጠቃለያ ፕሮገራሙ የተገኙት የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃ/ማርያም እንደተናገሩት እንደ ተቋም በርካታ ፈተናዎችን አልፈን የተቋሙን ገጽታ የቀየርን ቢሆንም አሁንም በአገልግሎት አሰጣጣችን እዚህም እዛም ህብረተሰቡ የሚማረርበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህንን መቀልበስ የምንችለው ደግሞ እኛው የተቋሙ ሰራተኞች እና አመራሮች ነን፡፡ የመታገያ መንገዱም ባለፉት ሳምንታት ስልጠና መሰረት የለውጥ መሳሪያዎችን ሳይሸራርፉ ተግባራዊ በማድረግ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

የዚህ ስልጠና ዋና ዓላማ የነበረው ሁሉም የተቋሙ ፈጻሚዎችና አመራሮች የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ፣ የሚስተዋሉ የአቅም ክፍተቶችን በመድፈን፣ ከኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር የራቀ  በአመለካከት፣ በክህሎት በዲሲፕሊን የተሻለ ሆኖ በመገኘት ህብረተሰቡ/ተገልጋዩ በአገልግሎት አሰጣጡ የሚረካበት ሰራዊት ሆኖ እንዲወጣ ማድረግ ነው፡፡