በአለም ባንክ የውሃ ሲንየር ግሎባል ዳይሬክተር ሳሮጅ ኩማር ጃህ የተመራው ልኡክ ዛሬ የድሬ እና ለገዳዲ ግድብ ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የሲቢሉ ግድብ ፕሮጀክት የፋይናንስ ጉዳይ እና በባንኩ የገንዘብ ድጋፍ የሚሰራውን የግድቡ ውሃ ማስተንፈሻ በሮች ጥገና ስራ ላይ ያተኮረ ውይይትም ተደርጓል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ዘሪሁን አባተ የአለም ባንክ ግሩፕ ለባለስልጣኑ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አድንቀው፤ በቀጣይ እንደ ከተማ ትልቅ ችግር የሆነውን ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል የሲቢሉ የውሃ ግድብ ፕሮጀክት ጥናት ቢጠናቀቅም የፍይናንስ ችግር ስለገጠመው ባንኩ በቀጣይ ቀዳሚ ፕሮጀክት አድርጎ እንዲደግፍ ጠይቀዋል፡፡

የሲቢሉ ግድብ 505,000 ሜትር ኪዩብ ውሃ በቀን መስጠት የሚችል ፕሮጀክት ሲሆን ከሶስት አመት በፊት በአለም ባንክ ድጋፍ ጥናቱ ተጠናቆ ፋይናንስ የማፈላለግ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ስራስኪያጁ አስታውሰዋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት በወቅቱ በነበረው የኢንጅነሪንግ ዋጋ ከ800 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት የሚፈልግ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡

በአለም ባንክ የውሃ ሲንየር ግሎባል ዳይሬክተር ሳሮጅ ኩማር ጃህ በበኩላቸው ግድቡ ከፍተኛ በጀት የሚፈልግ በመሆኑ ከባለስልጣኑ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሀገሪቱ ፋይናንስ ሚኒስቴር ጋር መነጋገር የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸው ፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አጀንዳ አድርገው እንደሚመክሩበት አመላክተዋል፡፡

ግድቡ ቢገነባ አሁን ያለውን የውሃ አቅርቦት 50 በመቶ ያሳድገዋል፡፡