የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በደሊቨሪ ዩኒት የታቀዱ ተግባራትን ከማሳካት አንፃር በውሃ አቅርቦት ዙሪያ እያጋጠሙ ባሉ ተግዳሮቶች ላይ በወር በአማካኝ ከ500 ሜትር ኪዩብ በላይ የባለስልጣኑን ውሃ ከሚጠቀሙ 150 ድርጅቶች ጋር ቅዳሜ ህዳር 30/2010ዓ.ም በጊዮን ሆቴል ውይይት አድርጓል፡፡

የውሃ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን መጨረሻ የከተማውን የውሃ አቅርቦት በቀን አንድ ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ሊያደርሱ የሚችሉ ፕሮጀክቶች በእቅድ ተይዘው እየተሠሩ መሆኑን የጠቀሱት የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለማሪያም በዘላቂነት የውሃ አቅርቦቱን የሚያሻሽሉ ፕሮጀክቶች እስኪጠናቀቁ ድረስ ከፍተኛ የውሃ ተጠቃሚዎች የራሳቸውን የውሃ ምንጭ በማጎልበትና ውሃ ቆጣቢ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የከተማውን የውሃ ስርጭቱን ፍትሃዊ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የከተማውን የውሃ አቅርቦት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ ቢመጣም የውሃ አቅርቦቱ ከከተማው የኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት ፍጥነት ጋር በእኩል መጠን ያደገ ባለመሆኑ በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ ከዚህም አንፃር በዕለቱ ግንዛቤ የተፈጠረላቸው ከፍተኛ የውሃ ተጠቃሚ ድርጅቶች የራሳቸውን የውሃ ጉድጓድ ለመቆፈር እና ውሃ ቆጣቢ ግብዓቶችን ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀው ባለስልጣኑ የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ባለስልጣኑ በአሁኑ ወቅት ከገፀ-ምድር እና ከርሰ ምድር የውሃ መገኛዎች ንፁህ ውሃ የማምረት አቅሙን በቀን 608 ሺህ ሜትር ኪዩብ አድርሷል፡፡ ሆኖም ግን የተፈጠረውን ውሃ የማምረት አቅም አሟጦ ከመጠቀም አንጻር የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ፣ የከርሰ ምድር ፓምፖች ብልሽት፣ የከርሰ ምድር የውሃ ምርት መጠን መቀነስ፣ የጉድጓድ ውሃ ጥራት ችግር እንዲሁም የውሃ መስመሮች መሰበር ተጨማሪ ተግዳሮቶች እንደሆኑበት ጠቅሷል፡፡