የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን እንደገና ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 10/1987 አንቀፅ 8 መሠረት በባለስልጣኑ የስልጣን እና የአገልግሎት ክልል ውስጥ ካልተፈቀደለት በስተቀር ማንም ሰው ውሃ ማምረት፣ ማከፋፈል፣ ለራሱም ሆነ ለሌላ አካል ማቅረብ እና ባለስልጣኑ የሚያቀርበውን ውሃ መሸጥ እንደማይችል ተደንግጓል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በዚሁ አዋጅ አንቀፅ 25 ንዕስ አንቀፅ 1 ለማንኛውም አገልግሎት የውሃ ጉድጓድ ለመቆፈር ወይም ለማስቆፈር የሚፈልግ ሰው ከባለስልጣኑ ፍቃድ ማግኘት አለበት፡፡
ሆኖም ግን በከተማችን አንዳንድ ቦታዎች ድርጅቶች እና ግለሰቦች ከባለስልጣኑ የውሃ መስመር፣ በድርጅት ከተቆፈረ ጉድጓድ እና ምንጩ ካልታወቀ ቦታ ውሃ በተሽከርካሪ በመቅዳት ለህብረተሰቡ እያዘዋወሩ በመሸጥ ላይ ይገኛሉ፡፡
በመሆኑም ውሃ በማከፋፈል እና በመሸጥ ላይ የምትገኙ አካላት ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ እያሳሰብን ጉድጓድ ቆፍረው ውሃ በሚያከፋፍሉም ሆነ በተሸከርካሪ እያዞሩ በሚሸጡ ግለሰብ እና ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ የምንወስድ መሆኑን እንገልፃለን፡፡
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን
የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች