የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን ፍሳሽ ቆሻሻን በዘመናዊ መንገድ ሰብስቦና አጣርቶ ከሚያስዎግድባቸው ፕሮጀክቶች መካከል የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ዋናውና ትልቁ ነው፡፡

ይህ ማጣሪያ ጣቢያ በቀን 100 ሺህ ሜ.ኩብ የማጣራት አቅም ያለው ሲሆን አሁን ላይ ግን እያጣራ ያለው በቀን 40 ሺህ ሜ.ኪዩብ ብቻ ነው፡፡

በዚህ በጀት አመት ግን በቀን 60 ሺህ ሜ.ኩብ እንዲያጣራ እየሠራ መሆኑን በባለስልጣኑ የፍሳሽ ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋለም ባዩ ተናግረዋል፡፡

ይህም በዋናነት ወደ ማጣሪያ ጣቢያው የሚገባውን ፍሳሽ ቆሻሻ ከፍ በማድረግ የሚከናወን ነው ያሉት አቶ ተስፋለም፤ የተለያዩ የቴክኒክ ስራዎች ከመስራት ባሻገር በዘመናዊ መንገድ ለማስዎገድ ቅጥያ ያልቀጠሉ ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሰረት የፍሳሽ መስመሩ ለሚያልፍባቸው አካባቢዎች ባለሥልጣኑ ከደንበኛው ቤት ሦስት ሜትር እስኪቀር ድረስ መስመሩን የሚዘረጋ ሲሆን ተጠቃሚ እንዲሆኑም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየሰራ ይገኛል ፡፡

ለዚህም እቅድ ስኬት ባለፈው የክረምት ወቅት ማጣሪያ ጣቢያው ለጎርፍ እና ለባእድ ነገሮች ተጋላጭ እንዳይሆን ክፍት የነበሩ ማንሆሎችን የመክደን፣ የጎርፍ ውሃ የሚያስገቡ መስመሮችን የመጠገን እና ተያያዥ ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ህብረተሰቡም የማጣሪያ ጣቢያውን ደህንነት ለመጠበቅ ከህገ-ወጥ ቅጥያ እና ባዕድ ነገሮችን በፍሳሽ መስመር ከመጨመር እንዲቆጠብ ባለስልጣኑ ጥሪውን ያስተላፋል፡፡