ስልጠናው በዓለም ባንክ በሁለተኛው የከተሞች የውሃ እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት አማካኝነት የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የአፈፃፀም አቅምን ለመገንባት በታቀደ ዕቅድ መሰረት የተዘጋጀ ነው፡፡

ከባለስልጣኑ የተውጣጡ ሃያ ባለሙዎች እና ሃላፊዎች ከሐምሌ 8–17 ቀን 2011 ዓ.ም ለአስር ተከታታይ ቀናት በህንድ ሃገር የአሰልጣኞች ስልጠና የሚወስዱ ሲሆን ከተመለሱ ቡኃላ በቀጣይ ሁለት ዓመታት የባለስልጣኑን አጠቃላይ ሠራተኞች የሚያሰለጥኑ ይሆናል፡፡

በኢሊሌ ሆቴል በተዘጋጀው የሽኝት ፕሮግራም ላይ የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ዘሪሁን አባተ ለስልጠኛው ዝግጅት እገዛ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው የተገኘውን የስልጠና አጋጣሚ ተጠቅሞ ባለስልጣኑን በመለወጥ የደንበኞቻችንን እርካታ ማሳደግ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

የቪቴንስ ኢቪደንስ ኢንተርናሽናል የሰሜን አፍሪካ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዳንኤል ጥሩነህ እንደተናገሩት የመሪነት ስልጠናው በሠራተኞች የሚመራ እና ሠራተኛው እራሱ የሚያቅፈው ዘለቄታዊ የሆነ እውነተኛ ለውጥ ለመፍጠር አጋዥ ነው፡፡

የአለም ባንክ ተወካይ የሆኑት አቶ አማኑኤል እንደገለፁት ስልጠናው በፕሮጀክት ደረጃ የተያዘ እና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለውጥ ለማምጣት ያለመ ሲሆን ባለስልጣኑ ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ አጋዥ የሆኑ ሰራተኞችን የሚፈጥር ነው፡፡

በዕለቱ ሠልጣኞች ስልጠናውን በአግባቡ በማጠናቀቅ የተጣለባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ስልጠናው በአለም ባንክ፣ እና በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን ከዚህ በፊት በአለም ባንክ ግሎባል ኢንሸቲቭ በህንድ እና በታንዛኒያ ተሰርቶበት ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ነው፡፡