የአዲስ አበባ ውሀ እና ፍሳሽ ባስልጣን ከ993ሺ ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸው የውሀ ፕሮጀክቶች ከ2900 በላይ አባወራች ተጠቃሚ አድርጓል፡፡
በለገዳዲ ለገጣፎ ከተማ አስተዳደር በበረህ ወረዳ ተገኝተን ያነጋገርናቸው ወ/ሮ የሺ ዋቅጅራ ከዚህ በፊት የምንጭ ውሃ ለመቅዳት በጣም ረጅም ርቀት ከመጓዝ ባለፈ በለሊት የሚደረግ ጉዞ ሴት ልጆቻቸውን ለአስገድዶ መደፈር ያጋለጥ እንደነበር አንስተው ፤የቦኖው በአቅራቢያቸው መገንባት ከስጋት፣ ከሸክም እና ከእንግልት እንደታደጋቸው ተናግረዋል ፡፡
የዚሁ አካባቢ ነዋሪ አቶ ግርማ ብሩ በበኩላቸው ከዚህ በፊት የሚጠቀሙት የምንጭ ውሃ ለውሀ ወለድ በሽታ እያጋለጣቸው እንደነበር አንስተው ፤አሁን ባስልጣኑ ባሰራው ቦኖ መጠቀም መጀመራቸው ከበሽታ ከመታደጉም ባለፈ ትልቅ እፎይታ እንደሰጣቸው ነው የነገሩን ፡፡
ቦኖው ከተሰራ ወዲህ ከምንጭ ውሀ ለመቅዳት ሲባል ከጅብ ጋር የሚደረገው ግብ ግብ አበቃ ያሉን ደግሞ ወ/ሮ ጫሊ ታዬ እና አቶ ተፈሪ ታደሰ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ለከተማው ነዋሪዎች እያቀረበ የሚገኘውን ንጹህ የመጠጥ ውሃ በውሃ ምንጭነት የሚያገለግሉት ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች የንጹህ መጠጥ ውሀ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ፕሪጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ የገኛል ፡፡
ባለስልጣኑ ከሚያሰራቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን ከፍተኛ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት በ2009 በጀት ዓመት ጀምሮ በለገዳዲ ለገጣፎ፣ በገላን እና ሰንዳፋ በኬ ከተማ አስተዳድር ስር ላሉ 3 የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች በድምሩ 7 የቦኖ ውሃ ተገንብቶ 2,974 አባዎራዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ለዚህም ፕሮጀክት ማሰሪያ ከ993,600 ብር በላይ ወጪ ተደርጓል፡፡ በማህሌት ሁነኛው
የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች