ቋሚ ኮሚቴዎቹ ሸጎሌ፣ ጊዮን በረኪና፣ፍራንሲስኮ፣ ሸገር መናፈሻ፣ እርሻ ሰብል እና ዳንሴ የተባሉ ጥልቅ የጉድጓድ ውሃ ፕሮጀክቶችን በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተመልክተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሞላ ንጉስ እና አባላቱ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን በከተማው የከፋ የውሃ ችግር ያለባቸው አከባቢዎችን በመለየት ችግሩን ለመቅረፍ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
በጉብኝቱም ውሃን የማልማት ስራ ከባድ እንደሆነ በተጨባጭ መመልከት መቻላቸውን ነው አባላቱ ያረጋገጡት ፡፡
ባለስልጣኑ የተጀመሩ ጉድጓዶች በቶሎ እንዲጠናቀቁ ፤ የተጠናቀቁት ደግሞ ወደ ተጠቃሚው በቶሎ እንዲደርሱ በማድረግ በኩል በርብርብ መስራት አለበት ብለዋል ፡፡
ውሃ የለማባቸው አካባቢዎች ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ ማድረግም እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡
በውሃ ፕሮጀክቶቹ አካባቢ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች በመዘዋወርም የፈረቃ ስርዓቱ በአግባቡ እየተተገበረ መሆኑንም ምልከታ አድርገዋል፡፡