የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በለገዳዲ ፣ ድሬ እና ገፈርሳ ግድቦች ዙሪያ የተፋሰስ ልማት ስራዎች እየሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዋና ስራ አስኪያጁ እና በየደረጃው ያሉ አመራሮች በዛሬው እለት ከዚህ ቀደም በግድቡ ዙሪያ የለሙ ገበያ ተኮር ፍራፍሬዎችን እና የባለስልጣኑ የችግኝ ማዘጋጃ ስፍራ ጎብኝተዋል፡፡በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት ተቋሙ ለአረንጓዴ ልማት ስራ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ የሚበረታታ እና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ ነው ብለዋል፡፡ባለስልጣኑ ከዚህ ቀደም የሎሚ፣ ብርትኳን ፣ ሮማእ እና አፕል ፍራፍሬዎች በማልማት ለ250 ሰዎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን በዚህ በጀት አመት የክረምት ወቅት ከ20 ሺህ በላይ የተለያዩ የዛፍ ችግኞችን ለተከላ አዘጋጅቷል፡፡