በባለስልጣኑ የአራዳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከኪራይ ቤቶች አስተዳደር ጋር የሚገባውን ውል በማስቀረትና ወሉን በቀጥታ ከተከራዮች ጋር በማድረግ በኪራይ ቤቶች አስተዳደር ህንፃዎች የሚኖሩ ደንበኞች ከውሃ አገልግሎት እና ክፍያ ጋር ሲያጋጥማቸው የነበረውን ውጣ ውረድ ለማስቀረት የሚያስችለል የማስተካከያ እያደረገ ነው ፡፡

የማስተካከያ ስራው በቅርንጫፉ ስር በሚገኙ 42 የኪራይ ቤት ህንፃዎች በዘፈቀደ በማድ ቤት እና ለንባብ አመቺ ባልሆነ ቦታ የተገጠሙትን ቆጣሪዎችን ከመኖሪያ ቤት ውጪ በመግጠም ንባቡንም በባለስላጣኑ ቆጣሪ አንባቢዎች አማካኝነት ለማከናወን የሚያስችል ነው፡፡

እየተከናወነ ያለው ተግባር የውሃ ብክነትን ከማስቀረቱ በተጨማሪ ደንበኞች ከባለስልጣኑ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲኖራቸው በማድረግ ካላስፈላጊ ውጣ ውረድ እንዲድኑ ከማረግ ባለፈ፤

በኪራይ ቤቶች አስተዳደር በኩል በየዓመቱ የሚደርስን እስከ 12 ሚሊየን ብር ያልተገባ ወጪ የሚያስቀር መሆኑን በአራዳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የውሃ ደንበኞች አገልግሎት የስራ ሂደት መሪ አቶ አቦማ ደፋልኝ ገልፀዋል፡፡

አቶ አቦማ እንዳብራሩት የአራዳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የውሃ ደንበኞች አገልግሎት በኪራይ ቤቶች ከሚኖሩ ደንበኞቹ በተደጋጋሚ ከቀርቡለት ቅሬታዎች በመነሳት በካሳንቺስ አከባቢ በ3 መኖሪያ ህንፃዎች ላይ ፍተሻ አድርጓል፡፡

በዚህም መሰረት 47 ነዋሪዎች በቤታቸው ውስጥ 71 ቆጣሪ ያላቸውና ከነዚህም ውስጥ 28 የሚሆኑት የውሃ አገልግሎት ክፍያ ከፍለው የማያውቁ ፤ ለሌሎች የቅሬታ ምንጭ በመሆናቸው ከኪራይ ቤቶች አስተዳደር ጋር በመነጋገር ነው የማስተካከያ እርምጃው የተጀመረው፡፡

ከዚህ በፊት ባለስልጣኑ ከኪራይ ቤቶች አስተዳደር ጋር በገባው ውል መሰረት ለአንድ ህንፃ አንድ የጋራ የውሃ ቆጣሪ በመስጠት በጥቅል ህንፃው የተጠቀመበትን የውሃ አገልግሎት ሂሳብ ሲያስከፍል ቆይቷል፡፡

የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ለተከራዮቹ የተናጠል ቆጣሪ በመስጠት እና በራሱ የቆጣሪ አንባቢዎች አማካኝነት ክፍያ ሲያሰበስብ የቆየ ሲሆን ይህ አሰራር የውሃ ሂሳባቸውን ባልከፈሉ ተከራዮች ችግር ምክኒያት ውሃ ሲቋረጥ ሃላፊነታቸውን የተወጡ ደንበኞችም አብረው ተጎጂ እንዲሆኑ አድርጓል ፡፡

አሁን የተዘረጋው አሰራር የየግል አገልግሎት ክፍያ የሚጠየቅ በመሆኑ ከዚህ በፊት የነበረውን ችግር እና ቅሬታ የሚፈታ ነው፡፡