በቀን 50 ሺ ሜትር ኪብ ውሃ የማምረት አቅም ያለው የኮዬ ፈጬ የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ግንባታ ሙሉ በሙሉ በመነጠቃቁ አገልግሎት ለመጀመር የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ የፕሮጀክት ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዓለም ባዩ ገለጹ፡፡
እንደ አቶ ተስፋዓለም ማብራሪያ ፕሮጀክቱ በኮዬፈጬ እና ቅሊንጦ አካባቢ በመገንባት ላይ ለሚገኙ ከ50 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከነባር አቃቂ ዌል ፊልድ ከርሰ ምድር ውሃ በማልማት የመጠጥ ውሃ ለማቅረብ ታስቦ ተግባራዊ የተደረገ ፕሮጀክት ነው፡፡
በዋነኝነት በዚህ ፕሮጀክት የ9 ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮና ፓምፕ ቴስት ስራ፣ የ8 ኪሎሜትር የዋና መስመር ዝርጋታ፣ የ23.2 ኪሎሜትር የስርጭት መስመር እና የ7.4 ኪሎሜትር የማሰባሰቢያ መስመር ዝርጋታ ተከናውኗል፡፡10000 ሜትር ኪዩብ እና 2500 ሜትር ኪብ የመያዝ አቅም ያላቸው የሁለት የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖች ግንባታም የዚሁ ፕሮጀክት አካል ነው፡፡
ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ በአጭር ጊዜ በ2010 ዓመት ብቻ ከከርሰ ምድር የውሃ መገኛዎች የኮንዶሚኒየም ሳይቶች እና ሌሎቸ የውሃ ዕጥረት ባለባቸው አካባቢዎች የኮዬ ፈጬን ፕሮጀክት ጨምሮ በድምሩ እስከ 70 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ በቀን በማምረት እና በማሰራጨት የከተማዋን ውሃ አቅርቦት ከፍ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡
አቶ ተስፋ ዓለም አያይዘውም በመካከለኛ እኛ በረጅም ጊዜ የከተማዋን የውሃ አቅርቦት ለማሳደግ የገርቢ ግድብ ጨምሮ የለገዳዲ ምዕራፍ ሁለት ጥልቅ ጉድጓድ ውሃ ልማት ፕሮጀክት፣ ሳውዝ አያት ኖርዝ ፋንታ የጉድጓድ ውሃ ልማት ፕሮጀክት፣የሰበታ ሆለታ የጉድጓድ ውሃ ልማት ፕሮጀክት እና ለረጅም ጊዜ ታሳቢ ተደርጎ የነበረውን ነገር ግን በአሁን ጊዜ የመካከለኛ ጊዜ ፍላጎትን ብቻ እንደሚያሳካ በጥናት የተረጋገጠውን የሲቢሉ የገጸ ምድር ውሃ ፕሮጀክት እና ሌሎችም ግንባታቸው የተጀመሩ እና በጥናት ላይ ያሉትን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች