የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ቅ/ጽ/ቤቱ ካሉት የደንበኞች ፎረም አባላት ውስጥ ከተወከሉ 50ዎቹ ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን በዋናነት የውሃ ስርጭት ላይ ትኩረት ያደረጉ ነበሩ።
ከተሳታፊዎቹ የውሃ ፈረቃ መዛባት፣ ውሃ በሚሸጡ ግለሰቦች ላይ መወሰድ ስላለበት እርምጃ፣ ከወቅታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የመጠጥ ውሃዎችን ደህንነት፣ በት/ቤቶች ትምህርት ሲጀምር ስለሚኖረው የውሃ ስርጭት እና የተቋሙን የመጠጥ ውሃ ሽያጭ ገቢ በተመለከተ ጥያቄዎች ቀርበው ከመድረኩ ሰፊ ማብራሪያ እና ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።
በተለይም በአባላቱ በተደጋጋሚ ስለተነሳው እና በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ስሙ መቀጠያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ስለተፈጠረው የውሃ ስርጭት መስተጓጐል አስመልክቶ በተሰጠው ምላሽ በአከባቢው ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ጉድጓዶች በፍጥነት ምርት መቀነስ( በሰኮንድ ከ8ሊትር የነበረው ወደ 1ሊትር ዝቅ በማለቱ )፣ የR3 የአይረን ማጣሪያ መሰንጠቅ እና ጨፌ የተባለው ምንጭ ባልታወቁ ሰዎች ከ9 ጊዜ በላይ መስመሩ የመበጠስ ችግር በመግጠሙ ምክኒያት ውሃ በአግባቡ ማድረስ አልተቻለም ነበር ፡፡
ቅ/ጽ/ቤቱ ካለው ተፈጥሯዊ የቦታ አቀማመጥ አኳያ ተደራራቢ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም መጻኢ ዕድሉ የተሻለ መሆኑን የጠቆሙት የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ አምባዬ አሰፋ በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 4 የእርሻ ሰብል መጋዘን ግቢ እና በሸገር መናፈሻ ተጨማሪ ውሃ የሚያመነጩ ጉድጓዶች በመቆፈር ላይ እንደሆኑ እንዲሁም እንደለገዳዲ ምዕራፍ ሁለት እና የገርቢ ግድብ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ችግሩን ከስሩ የሚቀርፍ እንደሆኑ አብራርተዋል።