የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለስልጣን ከሰጠው ኃላፊነት አንዱ እና ዋነኛው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ንፁህ የመጠጥ ውኃን ለነዋሪ እንዲያዳርስ ነው፡፡

ባለስልጣኑ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ንፁህ የመጠጥ ውኃ አምርቶ ከማሰራጨት ባለፈ በየቀኑ ከየአካባቢው የውኃ ናሙናዎችን በመውሰድ በላቦራቶሪ ምርመራ የጥራት ደረጃውን ይፈትሻል፡፡

ፍተሻ ከሚደረግባቸው የውኃ ናሙናዎች መካከል የብክለት ምልክት ቢያጋጥም ባለስልጣኑ አፋጣኝ ማስተካከያ ያደርጋል፡፡

ይህንኑ ተግባር በራሱ ከሚያደርጋቸው ፍተሻዎች በተጓዳኝ በመስመር ስብራት እና መሰል ችግሮች ብክለት ሲያጋጥም በህብረተሰቡ የሚሰጠውን ጥቆማ በመቀበል እና ፍተሻ በማድረግ የማስተካከያ ስራ ይሰራል፡፡

ያም ሆኖ ግን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ማንነታቸው በውል የማይታወቅ ግለሰቦች በየቤቱ እየዞሩ ባለስልጣኑ ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በተለያዩ ኬሚካሎች አክሞ የሚያሰራጨውን ውኃ ጥራት እንደሌለው በመንገር በህብረተሰቡ ላይ ውዥንብር እየፈጠሩ መሆናቸውን ደርሶበታል፡፡

ህብረተሰቡ እነዚህ ህገ ወጥ ግለሰቦች ከባለስልጣኑ ዕውቅና ውጪ መሆናቸውን ተረድቶ የሚያሰራጩትን የተሳሳተ መረጃ ይዞ እንዳይደናገር ያሳስባል፡፡

ህገ ወጥ ግለሰቦቹ በህግ አግባብ የሚጠየቁበት ሁኔታ ስለሚኖር እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ የባለስልጣኑ ደንበኞች በነፃ የስልክ መስመር 906 በመደወል ጥቆማ በመስጠት እንድትተባሩ ይጠይቃል ፡፡
በተጨማሪም በ 0911 86 86 27 ላይ በመደወል ጥቆማውን ማድረስ ይቻላል፡፡