የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የውሃ ብክነትን በመቀነስ የውሃ ስርጭቱን ለማስተካከል የሚያስችል ስምምነት ማያ ኮርፖሬሽን ከተባለ የሉዘንበርግ ድርጅት ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡
የከተሞች ውሃ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ሁለተኛው ምዕፍ አካል የሆነው ይህ ስምምነት አጠቃላይ ወጪው 8 መቶ ሚሊየን 487 ሺህ 107 ብር ሲሆን በአራት አመት ከ2 ወር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው፡፡
ስምምነቱ በጉርድ ሾላ እና ለሚ ኩራ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በተለዩ 25 ቀጠናዎች ማለትም በየካ አባዶ፣ የካ አያት፣ ፋኑኤል፣ ቦሌ አያት እና ቦሌ አረብሳ አከባቢ በሚገኙ የውሃ ስርጭት መስመሮች ላይ የዲዛይን ስራ በመስራት እያጋጠመ ያለውን የውሃ ብክነት በመቀነስ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ነው፡፡
የተፈረመው ስምምነት አፈፃፀምን መሰረት ያደረገ (Performance based contract) ሲሆን ከ37 ሺህ 500 በላይ ደንበኞች በሚገኙበት አከባቢዎች ያረጁ የውሃ መስመሮችን፣ የውሃ ቆጣሪዎችንና መገጣጠሚያዎችን በመቀየር፣ የደንበኞችን መረጃ በማዘመን እና የዕውቀት ሽግግርን በማድረግ የውሃ ስርጭት መረቡን የሚስተካክል እና ሲባክን የነበረውን ንፁህ የመጠጥ ውሃ የሚያድን ነው፡፡
ባለስልጣኑ ከሚያመርተው ውስጥ በስርጭት ላይ የሚባክንበትን ውሃ ለማዳን በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነው፡፡