ባለስልጣኑ ከባለፉት 10 ዓመታት ጀምሮ የከተማዋን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሳደግ እና የህብረተሰቡን ፍላጎት በአግባቡ ለማሟላት ነባር እና አዳዲስ የከርሠ ምድርና የገፀ ምድር የውሃ መገኛ ምንጮችን በማስፋፋት ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች አከናውኗል፡፡

ከተከናወኑ ዋና ዋና ፕሮጀክቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ የገፈርሳ ግድብ ማሻሻያ፣ የለገዳዲ ግድብ ማስፋፊያ እና የውኃ እጥረት በሚታይባቸው የተለያዩ የከተማዋ ኪስ ቦታዎች (Pocket Area) የተካሄዱ የጉድጓድ ቁፋሮ ፕሮጀክት ይገኛሉ፡፡

በእነዚህ የማስፋፈፊያ ፕሮጀክቶች አማካይነትም የከተማዋን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ማሳደግ ተችሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በጥናት ከተለዩ 4 ዌል ፊልዶች በተጨማሪ በአጭር ጊዜ ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡና የተጀመረውን ማስቀጠል የሚያስችሉ የተለያዩ የከርሰ ምድር ውኃ ልማት ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ትግበራ ተገብቷል፡፡

ከእነዚህ ፕሮጅክቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ በቀን 50ሺህ ሜ.ኩብ ውኃ የሚያመርተው የኮዬ ፈጬና ቅሊንጦ ኮንዶሚኒየም አካባቢ፣ በቀን 68 ሺህ ሜ.ኩብ ውኃ የሚያመርተው የሳውዝ አያት ኖርዝ ፋንታ እና በቀን 86 ሺህ ሜ.ኩ የሚያመርተው የለገዳዲ ዌል ፊልድ ግንባታዎች ሲሆኑ፣ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ የባለስልጣኑን ውሃ የማምረት አቅም ከፍ በማድረግ በተለይም በሰሜኑ የከተማዋ ክፍል የሚስተዋለውን የውሃ ችግር በመፍታት ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል፡፡