የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ማስፋፊያ ግንባታ  ተጠናቆ  አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በፕሮጀክት ጽ/ቤት የፍሳሽ ፕሮጀክት ዲዛይንና ቁጥጥር የሥራ ሂደት መሪ አቶ አብዱልሀኪም ከድር ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ አብዱልሀኪም ማብራሪያ ነባር የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎችን በማሻሻልና በማስፋፋት እንዲሁም ተጨማሪ አዳዲስ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያዎችን በመገንባት የተሰበሰበውን ፍሳሽ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አጣርቶ ለማስወገድ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር የሚያስችሉ የካፒታል ፕሮጀክቶች ተቀርጸው በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

ከፕሮጀክቶቹ አንዱ በሆነው የቃሊቲ ተፋሰስ ደግሞ ከአለም ባንክ በተገኘ ብድር የቃሊቲን ማጣሪያ ጣቢያ አቅም አሁን ካለበት 7500 ሜ.ኩብ በቀን ወደ 100 ሺህ ሜ.ኩብ በቀን በማሳደግ በተፋሰሱ ስር የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የሚያስተናግድ አቅም ለመፍጠር የሚያስችል የማስፋፊያ ሥራ ለማካሄድ በእቅድ ተይዞ ሲከናወን ነበር፡፡ ይህ ኘሮጀክት የአዲስ ከተማ፣ ፒያሳ፣ ሽሮሜዳ፣ ስታዲየም፣ አዲሱ ገበያ፣ አፍንጮ በር፣ አራት ኪሎ፣ ካዛንቺስ፣ ቄራ እና አጐራባች አካባቢዎች ለሚኖሩ 2.2 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጐች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ነው፡፡ ፕሮጀክቱ 2 ቢሊዮን ብር የፈጀ  ሲሆን ከአለም ባንክ በተገኘ የ100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር ዴኒስ እና አክተር በተሰኙ የቤልጂየም እና የግሪክ ስራ ተቋራጮች የተከናወነ ነው፡፡

ባለሥልጣን መ/ቤቱ ባዘጋጀው የ 5 ዓመት ሮድ ማፕ ከተማዋን በሦስት ተፋሰሶች ማለትም አቃቂ ተፋሰስ፣ ቃሊቲ ተፋሰስ እና ምስራቅ ተፋሰስ እንድትከፈል ተደርጎ በእያንዳንዱ ተፋሰስ የሚሰሩ ስራዎች ዝርዝር የፕሮጀክት ስራዎች እቅድ ወጥቶ ሰፊ እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡